በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የተመራ ልዑካን ቡድን በ146ኛው የዓለም የፓርላማ ኅብረት (IPU) ስብሰባ ላይ እየተሳተፈ ነው ።

41
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የተመራ ልዑካን ቡድን በ146ኛው የዓለም የፓርላማ ኅብረት (IPU) ስብሰባ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
አፈ-ጉባኤው በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ሰላምና ደኅንነትን ማስፈን ለዲሞክራሲ ለእድገትና ሰብዓዊ መብቶችን ለማስጠበቅ እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ቀጣናዊ እና አሁናዊ ኹኔታዎችን በሚመለከት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭቶችና በቀጠናው በርካታ ችግሮች እንደተደቀኑበት ገልጸው፣ ይህንንም ለመፍታት ዓለም አቀፍ ጥረትና ትብብር የሚያስፈልግ መሆኑን አፈ ጉባኤው ገልጸዋል።
አፈ- ጉባኤው፣ ኢትዮጵያ የበርካታ ብዝሃ ማንነት ሀገር መሆኗን ገልጸው፣ በሁሉም መስክ የሚስተዋሉ ልዩነቶችን በውይይትና በንግግር ለመፍታት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አቋቁማ ለጠንካራ ሀገራዊ መንግሥት ግንባታና ዘላቂ ሰላም እየሠራች መኾኑን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾን ለዚህም በባለፉት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራን በመተግበር ባለፉት አራት አመታት ከ25 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በማሳተፍ 25 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መትከሏን ፤ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ሁለንተናዊ የኢትዮጵያ ወሳኝ ተግባር መኾኑን ዓለም በተሞክሮነት እንዲማርበት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሻሻል እና ለመጨመር በልዩ ልዩ መሰኮች በርካታ የሪፎርም ሥራዎች ማከናወኗን ለማሳያም የሴቶች የፓርላማ ተሳትፎ፣ ሴቶች ከወረዳ እስከ ፌደራል መንግሥት ባሉ የኃላፊነት ቦታዎች ያላቸውን የፖለቲካ ውክልና በተለይም በፌደራል ሚኒስትር መሥሪያቶች ሴቶችን በኃላፊነት ወደፊት መምጣት የሀገራዊ ለውጡ ውጤት መኾኑን በንግግራቸው አስረድተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!