በፈረቃ ለማስተማርም የክፍል እጥረት ፈተና እንደሚሆንበት መምሪያው አስታወቀ፡፡

0
173

ባሕር ዳር፡ መስከረም 07/2013ዓ.ም (አብመድ) ‹‹ለኮሮናቫይረስ አጋላጭ ባልሆነ መንገድ የዛፍ ጥላ እና የዳስ ትምህርት ቤቶችን አዘጋጃለሁ›› ሲል የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

በ115 አንደኛ ደረጃና 10 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በሚከላከል መልኩ በፈረቃ ለማስተማር የክፍል እጥረት መኖሩን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

የብሔረሰብ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ገብረሕይወት አዱኛ የ2013 የትምህርት ዘመን ማስጀመሪያ የቅድመ ምዝገባ ሥራዎች ከኮሮናቫይረስ አጋላጭ ባልሆነ መንገድ በጥንቃቄ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአስተዳደሩ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በአንድ ክፍል 30 ተማሪዎችን ለማስተማር ዕቅድ መያዙንም ገልጸዋል፡፡

ኃላፊው በብሔረሰብ አስተዳደሩ 273 የመጀመሪያ ደረጃና 24 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህም 158 የአንደኛና 14 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቻ በፈረቃ ለማስተማር ምቹ ሁኔታ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ 115 አንደኛ ደረጃና 10 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በፈረቃ ለማስተማር የክፍል እጥረት ያለባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በሁሉም የክፍል ደረጃ በፈረቃ ለማስተማር በተያዘው እቅድ የክፍል እጥረት ላለባቸው ትምህርት ቤቶች እንደአማራጭ የዛፍ ጥላ ስርን እና የዳስ ላይ ክፍሎችን ምቹ አድርጎ ለማዘጋጀት በዕቅድ መያዙንም አስታውቀዋል፡፡

የወንበርና የዴስክ እጥረቶችን ለመፍታትም ከአካባቢው የሚገኙ ጥሬ ዕቃዎችን የተማሪ ወላጆች እና በጎ አድራጊዎች እንዲያበረክቱ ቅስቀሳዎችን እንደሚያደርጉ አቶ ገብረሕይወት ተናግረዋል፡፡
በብሔረሰብ አስተዳደሩ በቅድመ መደበኛ 20 ሺህ 840፣ ከ1-8 ክፍል 133 ሺህ 920 እና ከ9-12ኛ ክፍል ደግሞ 20 ሺህ ተማሪዎች ለማስተማር ዕቅድ መያዙን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በብሔረሰብ አስተዳደሩ የተማሪ ክፍል ጥምርታው እንደየአካባቢው ከአንድ ከፍል ለ19 አንስቶ እስከ አንድ ክፍል ለ120 እንደሚደርስ አስታውሰዋል፡፡

የ2013 የትምህርት ዘመን ሲጀመር ኳራንታይን ሆነው የቆዩ ክፍሎች በፀረ ተሕዋስ ኬሚካል እንዲጸዱ ማድረግ፣ የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ እና የሚመከሩ የኮሮናቫይረስ መከላከያ ግብዓት እንዲቀርብ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በቅርበት እንዲሚሠሩም አቶ ገብረሕይወት ተናግረዋል፡፡

በብሔረሰብ አስተዳደሩ በኽምጠኛ ቋንቋ የሚሰጡ ትምህርቶች በበጀት እጥረት ምክንያት ከ2012 የትምህርት ዘመን ጀምሮ የመጻሕፍት እጥረት እንደነበራቸው ያስታወሱት አቶ ገብረሕይወት ዘግይተው በማሳወቃቸው እስካሁን ባይደርስም በቅርቡ እንደሚደርስ ተስፋ ማድረጋቸውን ለአብመድ ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here