ባሕር ዳር:መጋቢት 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሠዎች ለሠዎች በጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት አንድ ሚሊዮን ዮሮ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ በአማራ እና በአፋር ለሚገኙ 12 ሆስፒታሎች እና 10 ጤና ጣቢያዎች የሚሰራጭ ድጋፍ አድርጓል።
የሠዎች ለሠዎች ሀገር አቀፍ ምክትል ተጠሪ ዶክተር አስናቀ ወርቁ ሠዎች ለሠዎች በጦርነት ለተጎዱ ተቋማት ያደረገው ይህ ድጋፍ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ተቋሙ ከዚህ ቀደምም በመጀመሪያ ዙር ለ8 ሆስፒታሎች ድጋፍ ያደረገ ሲሆን በሁለተኛ ዙር ለ12 ሆስፒታሎች ድጋፉን ማድረጉን ዶክተር አስናቀ አስታውሰዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል፡፡
ሰዎች ለሰዎች የሚያደርገውን ድጋፍ በመቀጠል በትግራይ ክልል የደረሰውን ጉዳት የዳሰሳ ጥናት በማድረግ ተቋሙ ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብቷል፡፡
ሰዎች ለሰዎች ላለፉት በርካታ ዓመታት ማኅበረሰብ ተኮር ፕሮጀክቶችን ሲተገብር እንደነበር ያስታወሱት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ ሲሆኑ ለተደረገው ድጋፍ በጤና ሚኒስቴር እና በተገልጋዩ ሕዝብ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የጤና ተቋማቱ ያጋጠማቸውን እጥረት በማሟላት ኅብረተሰቡን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ የህክምና መሳሪያዎቹ ጥራት ቀጣይነት እንዲኖራቸው በማሰብ ሰዎች ለሰዎች ለአንድ ዓመት የሚሆን መለዋወጫ ግብአቶችን ያቀርባል፡፡
የህክምና ቁሳቁሱን ጤና ሚኒስቴር ከቀረጥ ነጻ ወደ ሃገር ቤት የሚገቡበትን መንገድ እንደሚያመቻችና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚጠበቅበትን የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ዶክተር አየለ በዝግጅቱ ላይ ተናግረዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!