ባሕር ዳር: ሕዳር 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው የዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ወገኖች ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡
በዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በብሔረሰብ አስተዳደሩ አሁንም ወደ ቀያቸው ባለመመለሳቸው እና ወደ ቀያቸው የተመለሱ ወገኖችም ሀብት ንብረታቸው በመዘረፉ ድጋፍ ይሻሉ፡፡
እመቤት ሸጋው ከምትወደው ቀየዋ ከቤተሰቦቿ ጋር ርቃ በወለህ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ መኖር ከጀመረች ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በቆይታዋም ችግራቸውን ታሳቢ ያደረገ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዳልኾነ ነው የተናገረችው፡፡ ወደሚወዷት ቀያቸው አሁንም ያልተመለሱት እመቤትና ቤተሰቦቿ በመጠለያ ውስጥ የሰው እጅ እያዩ ኑሯቸውን እየገፉ ነው፡፡ ቀያቸው ሰላም ከኾነ ወደ ቀያቸው መመለስን እንደሚናፍቁ እና ድጋፍ እንዲደረግላቸውም ጠይቃለች፡፡
አቶ ክፍሌ አረቄም ሰባት ቤተሰቦቻቸውን ይዘው በወለህ መጠለያ ውስጥ የሚኖሩ አባ ወራ ናቸው፡፡ ቀያቸውን ለቅቀው ከወጡ ረዘም ያለ ጊዜ ኾኗቸዋል፡፡ ወደ አካባቢያቸው ባለመመለሳቸው ችግር ውስጥ መኾናቸውን አስረድተዋል፡፡ በመጠለያ ውስጥ በቂ የሚባል ድጋፍ እየተደረገላቸው አለመኾኑንም ነግረውናል፡፡ ሰባት ቤተሰብ ይዞ በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ህይወትን መግፋት ከባድ እንደኾነባቸውም ገልጸዋል፡፡ “ሰላም ኾኖ ወደ ቤታችን መሄድ እንፈልጋለን፣ ነገር ግን ቤታችን ተዘርፏል፣ እንጨቱን ሳይቀር ወስደውታል፣ ቆርቆሮውን እየገነጠሉ ዘርፈውታል፣ አላረስንም፣ ራሳችን እስክንችል ድረስ ድጋፍ ካልተደረገልን ችግር ውስጥ ነን” ነው ያሉት፡፡
የወለህ መጠለያ ጣቢያ አስተባባሪ ዓለሙ በላይ ለተፈናቃይ ወገኖች እየደረሰ ያለው ድጋፍ አነስተኛ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ያልተቋረጠ እና ፍትሐዊ የኾነ ክፍፍል ሊደረግ ይገባልም ብለዋል፡፡
የዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ ወይዘሮ ዝናሽ ወርቁ በብሔረሰብ አስተዳደሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች አሁንም ወደቀያቸው አለመመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡ በብሔረሰብ አስተዳደሩ ሰላም ወደ አለባቸው አካባቢዎች ወገኖችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ሥራ መሠራቱን ነው የተናሩት፡፡ በብሔረሰብ አስተዳደሩ አሁንም በተለያዩ ምክንያቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች መመለስ አለመቻላቸውንም ገልጸዋል፡፡
አካባቢያቸው ሰላም ኾኖ ወደ ቀያቸው የተመለሱ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም ጥረት እያደረጉ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ አሁንም በመጠለያ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ወገኖች አስቸኳይ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡ በብሔረሰብ አስተዳደሩ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ችግሩን ታሳቢ ያደረገ አለመኾኑንም አስታውቀዋል፡፡
ወገኖችን ወደ ቀያቸው እንመልሳን እየተባለ በመጠለያ ውስጥ ሊደረግላቸው የሚገባው ድጋፍ መቀነሱንም ገልጸዋል፡፡ በቀያቸው ሰላም ሳይረጋገጥ ወገኖችን መመለስ እንደማይቻልም ተናግረዋል፡፡ በመጠለያ ጣቢያ ቀዬውን እንደለቀቀ ዜጋ የሚገባቸው ድጋፍ እየተደረገ አይደለምም ነው ያሉት፡፡
በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከተመለሱት ወገኖች ይልቅ ያልተመለሱት እንደሚልቁም አስታውቀዋል፡፡ ድንገተኛ ድጋፍ ሊደረግላቸው የሚገቡ ወገኖችም መረሳት የለባቸውም ነው ያሉት፡፡ በመጠለያ ውስጥ ሲደረግ የነበረው ድጋፍ መቀነሱንም ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ ድንገተኛ የሚባል ድጋፍ መቆሙንም ተናግረዋል፡፡ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ አካላትም መቀነሳቸውን ነው የገለጹት፡፡ ወደ ቀያቸው ያልተመለሱት ብቻ ሳይኾን ወደ ቀያቸው የተመለሱትም ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡
የሚደረገው ድጋፍም ከተጎጂው ሕዝብ ጋር የተመጣጠነ እንዳልኾነም አስታውቀዋል፡፡ ተፈናቃይ ወገኖቹ ቤትና ንብረታቸው የተዘረፈባቸው እና የወደማቸው መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ መንግሥት አሁንም ድንገተኛ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡ ወደ ቀያቸው የሚመለሱ ወገኖችም እንደ አዲስ ሕይወትን የሚጀምሩ እንጂ ጥሪት የሌላቸው ስለመኾናቸውም ነው ያስገነዘቡት፡፡
ባላሀብቶች ለተጎዱ ወገኖች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡ መንግሥት ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር ሰላም የኾነ አካባቢ መፍጠር እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያ ተወካይ ዳይሬክተር ጌቴ ምህረቴ በአማራ ክልል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል፡፡ እየተደረገ ያለው ድጋፍ መቆራረጥ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡ ለተፈናቃይ ወገኖች የሚበቃ ድጋፍ በሚፈለገው ልክ ደርሷል ማለት እንደማይቻልም አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ በነበረው ጦርነት ከተፈናቀሉት በተጨማሪ ከሌሎች ክልሎች የመጡ ተፈናቃይ ወገኖች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡ አሁንም ወደ ቀያቸው ላልተመለሱ ወገኖች በቂ በሚባል ደረጃ ባይኾንም ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ይህም ካለው የሀብት እጥረት ጋር በተያያዘ ያገጠመ መኾኑን ነው ያነሱት፡፡
ወደ ቀያቸው የተመለሱ ወገኖችን በዘላቂነት ማቋቋም እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ወገኖችን በዘላቂነት ማቋቋም የሚያስችል ኮሚቴ መቋቋሙንም አስታውቀዋል፡፡ ሙሉ የኾነ ድጋፍ ባይኾንም ያለውን እያደረሱ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተቸገሩ ወገኖች ችግር የእኔ ችግር ነው ብሎ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን የተጎዱ ወገኖችን እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በክልሉ 8 ነጥብ 9 ሚሊዮን ወገኖች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ነው የተናገሩት፡፡ ነገር ግን የአቅም ችግር በመኖሩ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎችን ብቻ ለመደገፍ መገደዳቸውን ነው የገለጹት፡፡
በአማራ ክልል ለድጋፍ 840 ሺህ ኩንታል በአንድ ወር ያስፈልጋል፡፡ አቅርቦቱ መንግሥት ብቻውን የሚቋቋመው ባለመሆኑ ባለሃብቶች እና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!