በጎንደር ከተማ ዘመናዊ የቄራ አገልግሎት ሊገነባ ነው፡፡

0
48
በጎንደር ከተማ ዘመናዊ የቄራ አገልግሎት ሊገነባ ነው፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ለዘመናዊ ቄራ አገልግሎት መስጫ ግንባታው ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ተበጅቶለታል። ዘመናዊ የቄራ አገልግሎት ግንባታንም የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር አስጀምረዋል፡፡
የርእሰ መስተዳድሩ በተቀናጀ የከተሞች ልማት ፕሮግራም ጎንደር ከተማ ከዓለም ባንክ በምታገኘው ገንዘብ የሚሠሩ ሥራዎች በጥራትና በፍጥነት ሊሠሩ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ የቄራ አገልግሎት ግንባታውም በአጭር ጊዜ ግንባታ እንዲጀመር አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ለቄራ አገልግሎት ግንባታው የቦታ ዝግጅት የጎንደር ከተማ አስተዳደርና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳደር ያሳዩት ትብብር መጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል።
የጎንደር ከተማ ከንቲባ ሞላ መልካሙ በበኩላቸው በከተማው ውስጥ ከ115 በላይ የመንገድ፣ የድልድይና ሌሎች የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች እየተከወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ አሁንም በተቀናጀ የከተሞች ልማት ፕሮግራም ዘመናዊ የቄራ አገልግሎት ግንባታ በአጭር ጊዜ እንደሚጀመር ተናግረዋል።
በጎንደር ከተማ የእንስሳት እርድ በባህላዊ መንገድ እየተፈፀመ መቆየቱ ትልቅ ችግር መሆኑን ጠቁመው ችግሩን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የጎንደር ከተማ አገልግሎትና አቅርቦት አስተዳድር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኮሎኔል ዘለቀ አለባቸው ኅብረተሰቡ ተገቢ የቄራ አገልግሎት ባለማግኘቱ ለተለያየ ችግር ሲጋለጥ እንደቆየ አንስተዋል፡፡ አዲሱ ዘመናዊ የቄራ አገልግሎት በከተማው የነበረውን የቄራ አገልግሎት ችግር ለመፍታት ያስችላል ነው ያሉት፡፡
አቶ ዘመነ መወሻና ወይዘሮ የሽ ደሴ የጎንደር ከተማ ነዋሪ ናቸው። ጎንደር ከተማ በስልጣኔ ቀዳሚ ከነበሩ ከተሞች መካከል ብትሆንም ለዓመታት የቄራ አገልግሎት ባለመኖሩ ሕዝቡ ለተለያየ የጤና ችግር ሲጋለጥ መቆየቱን ተናግረዋል።
የቄራ አገልግሎት ቡድን መሪ ዶክተር መላኩ አየልኝ በከተማው ጤናቸው ያልተረጋገጡ የእርድ ከብቶች በየቦታው በልማዳዊ መንገድ እየታረዱ ለአገልግሎት ሲቀርቡ መቆየቱንና ሕዝቡም አማራጭ በማጣት ሲቸገር መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ፍጹምያለምብርሃን ገብሩ – ከጎንደር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here