በጎንደር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ መሠረተ ልማቶች በተሻለ አፈጻጸም ላይ መሆናቸውን የሥራ ኃላፊዎች ተናገሩ፡፡

214

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች በከተማዋ እና አካባቢው እየተገነቡ የሚገኙና የተጠናቀቁ መሠረተ ልማቶችን ዛሬ ጎብኝተዋል።

በከተማዋ በበጀት ዓመቱ 77 ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ ናቸው፡፡ ፕሮጀክቶቹ በክልል፣ በፌዴራል የበጀት ምንጭ እንዲሁም ከዓለም ባንክና ከሌሎች ድርጅቶች በተገኙ ድጋፎች ነው እየተገነቡ የሚገኙት፡፡ በከተማዋ እየተገነቡ ያሉት 23 የጌጠኛ መንገድ ፕሮጀክቶች፣ አምስት የጠጠር መንገዶች፣ ስድስት መካከለኛና 20 አነስተኛ ድልድዮች ናቸው። የድልድዮች አፈጻጸምም ከ75 ከመቶ በላይ መድረሱ ነው የተገለጸው።

በበጀት ዓመቱ ተጀምረው የተጠናቀቁ የመንገድ ግንባታዎች፣ ዘመናዊ የመሰብሰቢያ አዳራሽና የትራፊክ መብራቶች እንዳሉም ታውቋል፡፡

በፊዴራል መንግሥት እየተገነቡ ካሉ ፕሮጀክቶች መካከል ግንባታው እንደዘገየ የተገለጸው የመገጭ ግድብ ግንባታም የጉብኝቱ አካል ነበር፡፡ በ5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር እየተገነባ ያለው የመገጭ ግድብ አሁን ላይ በልዩ ትኩረት እየተገነባ፣ በተያዘው ዓመትም በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ ሥራው አሁን ላይ 67 ነጥብ 8 በመቶ እንደደረሰና በቀጣዩ ዓመት አጋማሽ ላይ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ መሐንዲስ ይርጋ አበባዬ አስታውቀዋል፡፡

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ማስተዋል ስዩም (ኢንጂነር) በበኩላቸው ፕሮጀክቱ አሁንም ክትትል እንደሚያስፈልገው፣ የውሃ ማጣሪያ ግንባታውም ከወዲሁ እንዲጀመር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በጎንደር ከተማና አካባቢዋ እየተሠሩ ያሉትን መሠረት ልማቶች የተመለከቱት የአማራ ክልል የከተማ ልማት፣ ቤቶች ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ምስራቅ ተፈራ በከተማዋ እየተሠሩ ያሉ የፌዴራልና የክልል ፕሮጀክቶች የሚበረታቱ መሆኑን ተናግረዋል። የክልሉ መንግሥት በሚችለው አቅም ሁሉ የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚሠራም አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ይርጋዓለም አስማማው-ከጎንደር