ባሕር ዳር:መጋቢት 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር – አዘዞ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ የአቅም ማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ።
ሥራ አስኪያጁ አቶ ይገርማል ማሩ እንዳስታወቁት የፓወር ትራንስፎርመር የአቅም ማሻሻያ ሥራው ጣቢያው የነበረውን 8 ነጥብ 4 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ወደ 31 ነጥብ 5 ሜጋ ቮልት አምፔር ለማሳደግ ያለመ ነው።
በኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው የነበሩት ትራንስፎርመሮች ከፍተኛ ጭነት ለመሸከም አቅም ያልነበራቸው እና ረጅም ርቀት ተጉዘው አገልግሎት ለመስጠት የሚያስቸግሩ በመሆኑ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ችግር ያጋጥም እንደነበር ሥራ አስኪያጁ አስታውሰዋል።
በከተማዋ አንገብጋቢ ጥያቄ ሆኖ የቆየውን የ33 ኪሎ ቮልት መስመር የኃይል መጨናነቅ ችግር ለመፍታት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ይገርማል ገለጻ ሪጅኑ ለከተማዋ የኃይል ፍላጎት ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት አቅሙ ከፍ ያለ ፓወር ትራንፎርመር በማምጣት የአቅም ማሻሻያ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።
የአቅም ማሻሻያ ሥራው በአራት ወጪ መስመሮች በ33 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመስጠት ትልቅ እገዛ ያደርጋል ያሉት ሥራ አስኪያጁ በከተማዋ የሚገኙ አዳዲስና ነባር ኢንዱስትሪዎች ለሚያቀርቧቸው የኃይል ፍላጎት ምላሽ ይሰጣል።
ከአቅም ማሻሻያ ሥራው ጎን ለጎን የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ያለበትን የሠራተኞች የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!