በጎርፍ መጥለቅለቅ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰብሎች ፈጥነው በሚደርሱ ሰብሎች ለመተካት እየሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

0
53
ባሕር ዳር፡ መስከረም 15/2013ዓ.ም (አብመድ) በደቡብ እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ብቻ በበረዶ እና ጣና ሞልቶ በመፍሰሱ ባደረሰው የውኃ መትለቅለቅ ምክንያት ከ16 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የለማ ሰብል ላይ ጉዳት መድረሱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡
በዚህም 31 ሺህ 882 የቤተሰብ አባላት ለችግር ተጋልጠዋል፡፡ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ የጥራጥሬ ሰብሎችን ለማልማት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን በቢሮው የሰብል ልማት እና ጥበቃ ባለሙያ ኤሊያስ በላይ ለአብመድ ገልጸዋል፡፡ ባለሙያው እንደገለጹት ጉዳት በደረሰባቸው ወረዳዎች የአርሶ አደሮች ፍላጎት ልየታ እየተሠራ ነው፡፡ ፍላጎትን መሠረት በማድረግ ግብዓት እንደሚሠራጭም ባለሙያው ገልጸዋል፡፡
ሌሎች ድርጅቶችም ምርጥ ዘር እና ሌሎች ግብዓቶችን እንዲያቀርቡ እየተሠራ መሆኑንም ባለሙያው አስታውቀዋል፡፡ ይሁን እንጅ ሁሉንም ግብዓት በመንግሥት ማቅረብ ስላማይቻል አርሶ አደሩ በእጁ የሚገኙ በጭር ጊዜ ሊደርሱ የሚችሉ የጥራጥሬ ሰብሎችን ፈጥኖ መዝራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ የተዘጉ የውኃ መውረጃ ማፋሰሻዎችን በመክፈት የማፋሰስ ሥራ መሥራት እንደሚገባም ባለሙያው አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ
ፎቶ፡- ከፋይል

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here