በግብጽ የተለያዩ ከተሞች በፕሬዝዳንት አል ሲሲ ላይ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ፡፡

0
117

ባሕር ዳር፡ መስከረም 10/2012 ዓ.ም (አብመድ) ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ የግብጽን በትረ ስልጣን ከተቆጣጠሩ 2014 (እ.አ.አ) ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል፡፡ በርካቶች ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተዋል፤ ፖሊስም አስለቃሽ ጋዝ በሰልፈኞቹ ላይ እየተኮሰ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች ሁስኒ ሙባረክን በአማጽ ወዳንበረከኩበት የታህሪር አደባባይ መውጣታቸውንና አል ሲሲም ከስልጣን እንዲወርዱ መጠየቃቸውን ነው ቢቢሲ የዘገበው፡፡

የታህሪር አደባባይ ሰልፈኞችን ተከትለው በመላ ሀገሪቱ ዜጎች ወደ አደባባይ መውጣታቸውም ነው የተነገረው፡፡

ሰልፈኞቹ አደባባይ የወጡት የፕሬዝዳንት አል ሲሲ መንግሥትን ‹‹በሙስና ተዘፍቋል›› በሚል ለመቃወም መሆኑም ተሰምቷል፡፡

ግብጻዊው ነጋዴና ተዋናይ ሙሐመድ አሊ በርካታ ግብጻውያን በድህነት ውስጥ እየኖሩ ባለስልጣናት በቅንጡ መኖሪያዎችና ሆቴሎች ሲንፈላሰሱ የሚያሳዩ ተከታታይ ቪዲዮዎችን ሲለቅቅ ከርሟል፤ ይህም ለተቃዋሚዎቹ ትልቅ ግብዓት መሆኑ ታውቋል፡፡ ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ግን ክሱን አጣጥለውታል፤ ‹‹ተራ ስም ማጥፋትና ውሸት ነው›› ብለውታል፡፡

ሰልፎች በአሌክሳንደሪያ እና ስዊዝ ከተሞችም መካሄዳቸው ነው የተዘገበው፡፡

በግብጽ በ2011 (እ.አ.አ) በተቀሰቀሰ ሕዝባዊ አመጽ ሀገሪቱን ለዓመታት የመሩት ሆስኒ ሙባረክ መወገዳቸውና የሙስሊም ወንድማማቾች ሕብረት በሙሐመድ ሙርሲ እየተመራ ወደ ስልጣን መምጣቱ የሚታወስ ነው፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ በአብዱል ፈታህ አል ሲሲ በተመራ ሌላ አመጽ የሙርሲ መንግሥት ከስልጣን ተወግዷል፡፡

ምንጭ፡- ቢቢሲ
በአብርሃም በዕውቀት