በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ፤ በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ፡፡

3128
በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ፤ በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 28/2013 ዓ.ም (አብመድ) የገና ጨዋታ መቸ እደተጀመረ የሚገልፅ ትክክለኛ መረጃ ባይኖርም ከክርስቶስ ልደት በፊት እረኞች በተለይ በበጋው ወቅት ከብት እየጠበቁ መስክ ላይ ይጫወቱት እንደነበር ይነገራል፡፡
ታድያ ይህ ጨዋታ አዝናኝና ተወዳጂ በመሆኑ ዘር፤ የሀብት ደረጃን፤ የሥራ ኀላፊነትና ሌሎች ልዩነቶች ሳይኖሩት ሁሉንም ሰው ያሳትፋል በዚህም “በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ” እየተባለ ይገጠምለታል፡፡ የእየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል የሚከበረው የገና ጨዋታ በሚዘወተርበት ወቅት በመሆኑም በዓሉ ሢከበር የገና ጨዋታም በስፋት ይካሄዳል፡፡
ታዲያ በዚህ በዓል ስለ ገና ጫዋታ ጥቂት መረጃ ልናደርሳቹዉ ወደናል፡፡ የገና ጫዋታ የኢትዮጵያ የባህል ስፖርት ፌደሬሽን ጥናት አካሂዶበት ሕግና ደንብ እንደተዘጋጀለት የአማራ ክልል ባህልና ስፖርት ፌደሬሽን የቀድሞ አመራር አቶ ዓለም ሁነኛው ነግረውናል፡፡
የኢትዮጵያ ባህልና ስፖርት ፌደሬሽን ከኢትዮጵያ ባህል ማዕከል ጋር በሀገሪቱ 2 መቶ 93 በህላዊ ስፖርቶች ላይ ጥናት አካሂዶ ነበር፡፡ ለአስራ አንዱ በተካሄደላቸው ጥናት ሕግና ደንብ ወጥቶላቸዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ የገና ጨዋታ አንዱ ነው፡፡
በ2006 ተከልሶ በተዘጋጀው የባህልና ስፖርት ሰነድ መሠረት የገና ጨዋታ ወደ 7 የሚደርሱ ሕግና ደንቦች ተዘጋጂቶለታል፡፡ አቶ ዓለም እዳብራሩት የተዘጋጀው ሕግና ደንብ የገና ጨዋታ ባህላዊ ይዘቱን ሳይለቅ በሕግና ደንብ እዲመራ የሚያደርግ ነው፡፡
የገና ጨዋታ ባዓለም ላይ በብዙዎች እንደሚወደደው የእግር ኳስ ጨዋታ የተመልካቾችን ቀልብ የሚስብ አዝናኝ ጨዋታ ነው፡፡ ታዲያ በገና ጨዋታ ደንብ መሠረት የመጫወቻ ሜዳው ምን መሆን እንዳለበት፤ የተጫዋቾች ብዛት፤ የዳኞች ብዛትና ኀላፊነት፤ ውጤት አሰጣጥና ሌሎች አስፈላጊ ደንቦች የተካተቱለት ነው፡፡
ፍጥነትን፤ አካላዊ ጥንካሬንና ትንፋሽን የሚጠይቀው የገና ጨዋታ ሳቢና ተወዳጂ እዲሆን ልክ እንደ እግር ኳስ ጨዋታ ደንቦቹ ይመሳሳላሉ፡፡ አቶ ዓለም እደነገሩን በመጀመሪያ ለገና ጨዋታ ሁለት ተጋጣሚ ቡድኖች ያስፈልጋሉ፤ ለጨዋታ የሚስፈልገው ሜዳም በደንብ ለጨዋታ ዝግጁ ይሆናል፡፡
ልክ እንደ እግር ኳስ ሜዳ የጎል ጠባቂ፤ የተከላካይ የአጥቂ፤ የማዕዘን መምቻ በኖራ ይሰመራል፡፡ የሜዳ ስፋቱ ደግሞ ርዝመቱ 90 ሜትር ጎኑ 50 ሜትር የሆነ ሜዳ ያስፈልጋል፡፡
በዚህ ሜዳ ውስጥ ለመጫወት ሁለቱ ተጋጣሚ ቡድኖች 15 ተጫዋቾችን ያቀርባሉ፤ አስሩ ሜዳ ውስጥ ገብተው የሚጫወቱ ሲሆን አምስቱ በተቀያሪ ወንበር ይቀመጣሉ፡፡ ጨዋታውን የሚመራ የማህል ዳኛ፤ ዳኛውን የሚያግዙ መስመር ዳኞች እዲሁም ተቀያሪ ተጫዋቾችን የሚቀይሩ ዳኞችም የገና ጨዋታ ተሳታፊወች ናቸው፡፡
ታዲያ ገና ጨዋታን ለመጫወት ሩር እየተባለች የምትጠራ ድቡልቡል መጫወቻ ያስፈልጋል፡፡ ክብደቷ እስከ 5 መቶ ግራም የሚመዝን ከእንጨት፤ ከጠፍር አሁን አሁን ደግሞ ከፕላስቲክ ይዘጋጃል፡፡ ድቡልቡል መጫወቻ ወይም ሩሩን ለመምታትና ወደ ተቃራኒ ቡድን ግብ ለማስገባት ልክ እደ ማንኪያ ቅርፅ ያለው ከ1ሜትር የማይበልጥ ቁመት ያለው የገና ዱላ ያስፈልጋል፡፡ የገና ዱላው ለሁሉም ተጨዋቾች በእኩል ቁመት የተዘጋጀ ሆኖ ይታደላል፡፡
ልዩነት አለመኖሩን ዳኛው የማረጋገጥ ኀላፊነት አለበት፡፡ ጫዋታው ሲጀመር ሁሉም ተጫዋቾች ተነፋነፍ የሚባለውን ባህለዊ ልብሳቸውን ለብሰው ቦታ ቦታቸውን ይይዛሉ አጥቂው ከአጥቂ፤ ተከላካይ እዲሁ በቦታው፣ በረኛውም በተጠንቀቅ በቦታው ይሰየማል፡፡
ጫዋታውን የሚያስጀምሩት ዳኛ ሶስት “ጊዜ እዚህ እሩር እዛ ገና ” ካለ በኋላ ጨዋታው ይጀመራል፡፡ በጨዋታው ሕግ መሰረት ሩሯን በእግርና በእጂ መንካት ነጥብ የስቀንሳል፡፡ ለ30 ደቂቃ በመጀመሪያው ምዕራፍ ይጫወታሉ ለ10 ደቂቃ እረፍት ከወሰዱ በኋላ የጫዋታ ሜዳ ተቀያይረው ሁለኛ አጋማሽ ጨዋታቸውን ያካሂዳሉ፡፡
ጨዋታው ለዋንጫ ወይም ለደረጃ ከሆነ ቡድኖቹ ካልተሸናነፉ ተጨማሪ ደቂቃ እዲጫወቱ ይደረጋል፡፡ በዚህም ካልተሸናነፉ የቅጣት ምት እየተሰጣቸው እስኪ ሸናነፉ ድረስ ይጫወታሉ፡፡
የገና ጨዋታ አካላዊ ጥናካሬና ፍጥነትን እዲሁም የብዙ ሰዎች ቀልብ የሚገዛ በመሆኑ ባህላዊ ይዘቱን ሳይለቅ በሕግና ደንብ መመራቱ አሁን በዓለም ላይ እግር ኳስ የደረሰበትን ተወዳጂነት ያመጣውን ኢኮኖሚያዊ ለውጥ በገና ጨዋታ ለማምጣት የሚያግዝ ይሆናል፡፡
የገና ጫዋታን ገና በዓል በሚከበርበት ወቅት ብቻ ከመጫወት ይልቅ ልክ እንደ እግር ኳስ እንዲዘወተር በማድረግ ለዓለም ማስተዋወቅ ስፖርቱ እንዲያድግ ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡
ዘጋቢ፡- ሸምስያ በሪሁን
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ