ደሴ :መጋቢት 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ቀለም ኢትዮጵያ የተሰኘ ሀገር በቀል መንግሥታዊ ያልኾነ ድርጅት በደቡብ ወሎ ዞን ለሚገኙ ለ694 አርሶ አደሮች አገልግሎት የሚሠጡ 148 የውኃ መሳቢያ ሞተር ፓምፖችን ድጋፍ አድርጓል፡፡ ፓምፖቹ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያላችው ናቸው።
ድጋፉ በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኙ 694 የቃሉ፣ ተሁለደሬ፣ ኩታበርና ደሴ ዙሪያ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተገልጿል።
አርሶ አደሮቹ የተደረገው ድጋፍ በመስኖ ለማልማት የነበረባቸውን የአቅም ውስንነት የሚቀርፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ቀለም ኢትዮጵያ ላደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።
የቀለም ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ አብዱል አዚዝ አራጌ እንደገለጹት ድጋፉ በዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮችን ታላሚ አድርጓል ብለዋል። አርሶ አደሮች በተደረገው ድጋፍ ጠንክረው በመሥራት ራሳቸውን እና ሀገራቸውን በምግብ እንዲችሉ አደራ ብለዋል፡፡
በርክክቡ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አዝመራው ተጫኔ ድጋፉ በተለይ ግብርናውን በማዘመን አርሶ አደሮች በዓመት ሁለት እና ከዚያ በላይ ጊዜ እንዲያመርቱ ያግዛል ብለዋል፡፡ ቀለም ኢትዮጵያ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል ።
ዘጋቢ፡- አበሻ አንለይ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!