በደረስጌ ማርያም ውስጥ ዘመናዊ ሙዚየም አየተገነባ መኾኑን የወረዳው ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

110
Made with LogoLicious Add Your Logo App
ደባርቅ: ሕዳር 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን ጃናሞራ ወረዳ ውስጥ በምትገኘው ደረስጌ ማርያም ገዳም ውስጥ ያሉ ታሪካዊ ቅርሶችን በዘመናዊ መልኩ ለመጠበቅ የሚያስችል ሙዚየም እየተገነባ መኾኑን የወረዳ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ገልጿል። ደረስጌ ማርያም የበርካታ ቅርሶች መገኛ ታሪካዊ ደብር ናት።

የደብሩ ዋና አስተዳዳሪ እና ታሪክ አዋቂ መጨኔ ጥጋቡ ቢምረው መረጃ እና ማስረጃን ከአፈ ታሪክ እያጣቀሱ እንደነገሩን ደረስጌ ማርያም የተመሰረተችው በ12ኛው ክፍለ ዘመን በአድያም ሰገድ ኢያሱ ነበር። የባለብዙ ታሪክ ባለቤቷ ደረስጌ ማርያም አሁን ያለውን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን እና ቅርስ ይዛ የታነጸችው ደግሞ በሰሜኑ ገዥ ራሥ ውቤ ሃይለማርያም ሲኾን ጊዜው በ1818 ነው ይላሉ መጨኔ ጥጋቡ።
ቦታው የኢትዮጵያውያን የአንድነት ፈር ቀዳጅ የኾኑት አጼ ቴዎድሮስ በአቡነ ሰላማ ተቀብተው ለንግሥና ከፍ ብለው የቆሙበትን ሰገነት የያዘም ነው። የሰገነቱን ግንብ ውቤ ሃይለማሪያም ለራሳቸው መንገሻ በማሰብ ያስገነቡት ነበር። ይሁን እንጅ የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ አልመው ከቋራ ወደ ሰሜን የተንቀሳቀሱት ደጃዝማች ካሳ የሰሜኑን ገዥ ራሥ ውቤን ማርከው በዚያ ሰገነት ላይ እራሳቸው “ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ” ተብለው ነገሱ። ይህ የኢትዮጵያውያን የአንድነት መንፈስ ውጥኑ የተመሰረተበት እና አጼ ቴዎድሮስ ከላዩ ላይ በከፍታ ቆመው ለንግሥና የተቀቡበት ታሪካዊ ግንብ በደረስጌ ማርያም ቅጥር ግቢ ውስጥ በክብር ቆሞ ይገኛል።

ሰገነቱ ፣ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ እና እቃ ቤቱ በሙሉ ውቤ ኀይለማርያም ቀደም ብለው ባሰባሰቧቸው ጥንታዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች የታጨቀ ነው። በስም ለመዘርዘር የሚያታክቱ፣ የጥንቱን ዘመን ከአሁኑ የሚያስተሳስሩ በርካታ ንዋየ ቅድሳት በዚያ አሉ። በወርቅ እና በብር የተንቆጠቆጡ ከበሮዎች፣ ከጎሽ ቀንድ የተሠሩ ዋንጫዎች፣ የንግሥና አክሊል ወዘተረፈ መገኛቸው ደረስጌ ማርያም ነው።
መጨኔ ጥጋቡ ቢምረው እንደተናገሩት የነዚህ ሁሉ ቅርሶች አያያዝ አይተኬነታቸውን ያገናዘበ አይደለም። ደኅንነቱ እና ንጽሕናው በአስተማማኝ ሁኔታ ባልተጠበቀ እቃ ክፍል ውስጥ ተከማችተው እርጥበት እና ምስጥ እየጎዳቸው ስለመኾኑም ነግረውናል። የአካባቢው ማኅበረሰብ በየተራ እየተቧደነ በሌሊትና በቀን ጥበቃ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
የጃናሞራ ወረዳ ባሕል ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወይዘሮ አምሳል ነጋ በደረስጌ ማርያም ውስጥ ለቱሪዝሙ ዘርፍ አይነተኛ ሚና ያላቸው ቅርሶች መኖራቸውን ገልጸዋል። እነዚኽን ቅርሶች በማስጎብኘት ገቢ ከማመንጨት በተጨማሪ ደኅንነታቸውን ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ወይዘሮ አምሳል ከዚኽ በፊት ቅርሶቹ በአግባቡ ተቀምጠው ለእይታ የሚቀርቡበት ሙዚየም እንዳልነበር ገልጸዋል። አሁን ላይ ግን የክልሉ መንግሥት በመደበው ገንዘብ እና በአካባቢው ነዋሪዎች ርብርብ የሙዚየሙ ግንባታ እንደተጀመረ አመላክተዋል። ይሁን እንጅ የተበጀተው ገንዘብ በቂ ባለመኾኑ እና የአካባቢው ነዋሪዎችን አቅምም በመፈተኑ የሙዚየሙ ግንባታ እንዳልተጠናቀቀ ገልጸዋል። ሙዚየሙ ተጠናቆ የሀገር እና የሕዝብ ሀብት የኾኑት የደረስጌ ማርያም ቅርሶች በሚመጥናቸው ቦታ ተቀምጠው እንዲጎበኙ ለማስቻል ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ኀላፊዋ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!