“በዚህ ታሪካዊ ቀን ኢትዮጵያችን አሸንፋለች” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

0
59

“በዚህ ታሪካዊ ቀን ኢትዮጵያችን አሸንፋለች” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) ሀገራዊ ምርጫውን አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የምርጫው ድምጽ አሰጣጥ ሂደት በሰላም በመጠናቀቁ እንኳን ደስ አለን!

የዛሬው ቀን ለመላው ኢትዮጵያን ታላቅ ቀን ነው።
ለዘመናት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማከናወን ስንናፍቅ
ኖረናል። እነሆ ጊዜው ደርሶ ያለምነውን ዛሬ ፈጽመናል። ዴሞክራሲ ለሀገራችን ምኞት ብቻ ሳይሆን
የታሪካችን አካል መሆኑን በዓለም ሕዝብ ፊት በግልጽ አሳይተናል። ከየትኛውም ወገን ያልሆነ ገለልተኛ
የምርጫ ቦርድ ተቋቁሞ፣ በአጭር ጊዜ ተዓማኒና ፍትሐዊ የሆነ ምርጫ አካሂደን በስኬት አጠናቅቀናል።
ከእንግዲህ የምርጫው አሸናፊ ማንም ይሁን ማን፣ በዛሬው ዕለት ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ ወጥተው ይወክሉናል የሚሏቸውን ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ በመምረጣቸው ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆናለች።
በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ብታልፍም በዚህ ታሪካዊ ቀን ኢትዮጵያችን አሸንፋለች። እንኳን ደስ አለን።

የኢትዮጵያ ታሪክ በሁለት ተቃራኒ የሉዓላዊነት እውነቶች የሚላጋ ነው። ቀዳሚው የሀገራችንን ሉዓላዊነት ከማንኛውም የውጭ ኃይል ተከላክለን ለዘመናት አስከብረናል። በዚህም የተነሣ ነጻነቷን የጠበቀችና ታፍራና ተከብራ የኖረች ሀገር መሥርተናል። በተቃራኒው የሕዝብን የሥልጣን ሉዓላዊነት ማስከበር አልቻልንም። የሕዝብን ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነትን ማረጋገጥ ባለመቻላችን፤ እሱን ተከትለው በሚመጡ ችግሮች ሀገራዊ ህልውናችን ለተደጋጋሚ አደጋ ተጋልጧል።

ይህን የታሪካችንን እውነታ የመቀየር አጋጣሚ በተደጋጋሚ አግኝተን ነበር። ግን አልተጠቀምንበትም።ሕዝብን ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት የሚያደርግ ዴሞክራሲያው ሥርዓት ውስጥ እንድንገባ ታሪክ ዛሬ ሌላ ዕድል ሰጥቶናል።

ወደ ዲሞክራሲ የሚደረግ ሽግግር ወደ ኋላ በሚስብ ያለፈ ኢ-ዴሞክራሲያዊነት እና ወደ ፊት በሚታይ አዲስ የዴሞክራሲ ብሩህ ተስፋ መካከል የሚገኝ ነው። ከሽግግሩ አልፎ ዴሞክራሲን በማይነቃነቅ መሠረት ላይ ማቆም የሚቻለው ወደ ኋላ የሚስበንን ኃይል ለመታገል በምንጨርሰው ኃይል ሳይሆን አዲስ በምንገነባው ሥርዓት ላይ ትኩረት በማድረግና እየተገነቡ የሚሄዱ ጠንካራ የዴሞክራሲ ጡቦችን በማስቀመጥ ነው።

ውድ ኢትዮጵያውያን!
እስካሁን በሀገራችን የተደረጉ ዴሞክራሲን የመትከልና የማጽናት ትግሎች ያለፈውን እና የነበረውን
በመታገል ስኬታማ ሆነው ነበር። አያስፈልግም የምንለውን ያለፈውን ሥርዓት ካስወገድን በኋላ ግን ለወደፊት የሚያስፈልገንን በሚገባ አንተክለውም፤ ተክለንም አናሳድገውም። በዚህም ምክንያት ከትግሉ
መነሻ እንጂ ከመድረሻው ላይ መቆም አልተቻለም። ትግላችን ሁሌም በእንጥልጥሉ የሚቋጭ፣ ለፍሬ
የማይበቃ፣ በአለፍንበት መንገድ ዳግም እንዳንመለስ የሚያደርገን አልሆነም። ለዴሞክራሲ ታግለን የዴሞክራሲን ችግኝ የመንከባከብ ፍላጎቱ አይኖረንም። በአንዲት ምሽት ዴሞክራሲ ሆኖ የሚያድር ሀገር እንደሌለ አውቀን ለዴሞክራሲ ግንባታ ወሳኝ የሆኑ ጡቦችን ችላ ሳንል አንዱን በሌላው ጡብ ላይ እየደረደርን መጓዝ መማር አለብን። ከዚህ አንጻር ሲታይ የዘንድሮው ምርጫ በብዙ መልኩ ለዴሞክራሲ ግንባታ ወሳኝ ከሆኑ እርምጃዎች እንደ አንዱ ስለሆነ ልምዶቻችን ወደፊት ለምናደርጋቸው እልፍ ምርጫዎች ጥሩ መነሻ ተደርገው መወሰድ አለባቸው።

የተከበራችሁ ተፎካካሪ ፓርቲዎች!
ለዚህ ምርጫ መሳካትና ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቅ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጫናዎችን ሁሉ ተቋቋማችኋል። ስሕተቶችን በማረምና በመታገሥ ከፍ ያለ ሚና ተጫውታችኋል። ለዚህም ያለኝን አክብሮት ሳልገልጽ አላልፍም። የሀገራችን ሁለንተናዊ ችግሮች ውስብስብና ተደራራቢ መሆናቸውን ተገንዝባችሁ፣ ምርጫም ችግሮቻችን ለመፍታት አንዱ መንገድ እንጂ በራሱ ብቸኛ መፍትሔ አለመሆኑን አምናችሁ፣ ለዴሞክራሲያዊ ልምምዳችን የመጀመሪያውን ጡብ በጋራ ስላስቀመጣችሁ ይኼንን ተግባራችሁን ታሪክሲዘክረው ይኖራል።

በምርጫው የትኛውም ፓርቲ ቢያሸንፍ፣ ሂደቱ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁ በራሱ ከአንድ
የምርጫ ዙር አሸናፊነት በላይ ነው። ይህም የዴሞክራሲ ልምምዳችንን አንድ ርምጃ ወደ ፊት የሚያስኬድ ስለሆነ ለሀገራችን ትልቅ ትርጉም ያለው ተግባር ነው።

የተከበራችሁ የምርጫ ቦርድ አመራሮችና ሠራተኞች፣

ይኼን ታሪካዊ ምርጫ ለማከናወን ኃላፊነት ስትረከቡ ነገሮች አልጋ በአልጋ እንደማይሆኑላችሁ ተገንዝባችሁ እንደሆነ ይታወቃል። ከዚህ ቀደም ያልነበረ ልምምድን የማምጣት፣ ከየአቅጣጫው በሚወረወሩ ዕንቅፋቶች ሳይበገሩ ገለልተኛ የምርጫ ማስፈጸሚያ ተቋም የመገንባት፣ ተአማኒና ዘላቂ የሆኑ አሠራሮችን ለሀገራችን የመዘርጋት አስደናቂ ጉዞ ተጉዛችኋል። ተጀምሮ እስኪያልቅ ሁሉንም ተፎካካሪዎች በእኩልነት ተመልክታችሁ፣ የአሠራር ግልጽነትን ፈጥራችሁ፣ ምርጫው ተአማኒነቱ
እንዲጠበቅ በማድረጋችሁ በዴሞክራሲያዊ ልምምዳችን ውስጥ ጉልህ አሻራ አኑራችኋል። ለዚህ ኢትዮጵያ ደጋግማ ታመሰግናችኋለች።

ሚዲያዎች፣ ታዛቢዎች፣ የሲቪክ ማኅበራትና አጋር አካላት ሁሉ፤

ምርጫው ነጻ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በማድረግ ከመነሻው እስከ ፍጻሜው የተጋችሁ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ በጎ ፈቃደኞች፣ ታዛቢዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ ሚዲያዎች፣ ጋዜጠኞች እና ሌሎችም ውጤቱ የእናንተም ነውና እንኳን ደስ አላችሁ። የምርጫው ሂደት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አሻራችሁን ያኖራችሁ ሁሉም አካላት በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይታሪክ ሠርታችኋል። አንዳንዶች ሸርተት ባሉበት ወቅት፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ሳትለዩ፣ የምናደርገው
የፖለቲካ ሽግግር እንዲሳካ አስተዋጽዖ ያደረጋችሁ ዓለም አቀፍ አጋር ሀገራትንና ተቋማትን ኢትዮጵያ
ታመሰግናችኋለች።

የጸጥታና ደኅንነት አካላት በሙሉ፤
የምርጫው ሂደት ከተጀመረበት ዕለት አንሥቶ በያቅጣጫው የተከፈተውን ፈተና በማርገብ፣ ጸጥታ
በማስከበር፤ ሕዝቡ ሰላምና ደኅንነት ተሰምቶት እንዲመርጥ ሌትና ቀን የለፋችሁ የጸጥታ ኃይሎች፤ በዚህ ወሳኝ ወቅት ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ ሕዝቦቿ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነታቸው እንዲረጋገጥ የከፈላችሁት መሥዋዕትነት በታሪክ የሚዘከር ነው።

በመጨረሻም፣ በቀጣይ ቀናት የድምፅ ቆጠራ ተካሂዶ ውጤት እስኪገለጽ ምንም ዓይነት ችግሮች
እንዳይፈጠሩ፣ እስካሁን በመጣንበት ሰላማዊ ሂደት እንድንቀጥል፣ ለሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪዬን
አቀርባለሁ። በአራቱም አቅጣጫ የሚኖረው ሕዝባችንም ከምርጫ አስፈጻሚዎች እና ከጸጥታ አካላት ጋር በመናበብ የተጀመረውን ሰላማዊ ምርጫ ከፍጻሜው እንዲደርስ መልካም ትብብራችሁ እንዳይለይ ስል ከታላቅ አክብሮት ጋር አሳስባለሁ።

በልዩ ልዩ ምክንያቶች ምርጫ ያልተደረገባቸውን አካባቢዎች ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ
መሠረት፣ ዛሬ በጀመርነው መልኩ ምርጫ እንዲደረግባቸው የሁሉንም አካላት የላቀ ርብርብ ይፈልጋል።የዚህኛው ስኬትም ለዚያኛው ብሩህ ተስፋ ነው።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ሰኔ 14፣ 2013 ዓ.ም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here