ባሕር ዳር: ግንቦት 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳደር ከፍተኛና መካከለኛ መሪዎች “ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን ” በሚል መሪ ሃሳብ በወቅታዊ ኹኔታዎችና የቀጣይ መፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ለተከታታይ ሦስት ቀናት የሚቆይ ውይይት ማካሄድ ጀምረዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ አለባቸው ገነቱ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በሕዝብ ዘንድ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ አሁን ላይ ከመቸውም ጊዜ በላይ የመሪዎች አንድነት የሚጠይቅበት ወቅት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎችን በትግል ሂደት ከመመለስ ባሻገር መሪዎች አካባቢያዊ የአስተሳሰብ ጉድለቶችን በማጥራት የመሪዎች አንድነትን በማሳደግ የሚገጥሙ ፈተናዎችን በድል ለመሻገር ወጥ አቋም የሚያዝበት ነው ብለዋል።
“የፖለቲካ ትግል ውጤታማ የሚኾነው ሀቀኛ ጥያቄዎች አግባብነት ባለው የትግል ስልት ሲመሩ ብቻ ነው” ያሉት ደግሞ የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አቶ መልካሙ ተሾመ ናቸው።
ክልሉ በተከታታይ ከፍተኛ መሪዎችን ጨምሮ በየደረጃው የሥራ ኀላፊዎች የሚገደሉበትና ይልቁንም የሃሳብ እና የፖለቲካ አሰላለፍ ነጻነትን የማይቀበል ጠላት አድርጎ የሚስል አስተሳሰብ እና ጽንፈኝነት የአማራን ሕዝብ ፖለቲካ ወደ ውድቀት የዳረገ ኾኖ መዝለቁን አንስተዋል።
በውይይቱም ከዚህ የአዙሪት አስተሳሰብ እና ጉዞ በመውጣት ድሎችንና ውድቀቶችን እንዲሁም እድሎችንና ስጋቶችን በመለዬት የተሟላ የፖለቲካና የጸጥታ ኹኔታ እንዲፈጠር፤ የሕዝባችን መሠረታዊ ጥያቄዎች ሕጋዊ ሥርዓታዊና መዋቅራዊ ምላሽ የሚያገኙበት ቀጣይ ትግልን በተመለከተ ኮንፈረንሱ የጋራ ግንዛቤ የምንይዝበት ነው ብለዋል።
በውይይቱ የተገኙት የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ አረጋ ከበደ የውይይቱ ዓላማ በክልሉ በተከታታይ እየገጠመ ያለውን ውስብስብ ችግሮች መንስኤ በመለየት መውጫ መንገዶችን በማስቀመጥ የጋራ አቋም ለመያዝ ያለመ ነው ብለዋል።
በተለይም የአማራን ሕዝብ ሰላምና ደኀንነት ለማስጠበቅ እየገጠሙ ያሉ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችን መለየት እንዲሁም በዘላቂነት የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግ ቀዳሚው ጉዳይ መኾኑን አንስተዋል።
ከተለያየ ወረዳና ከተማ አሥተዳደር የመጡ የውይይቱ ተሳታፊ መሪዎች ኮንፈረንሱ ሀገራዊ ፣ ክልላዊና አካባቢያዊ ወቅታዊ ኹኔታዎችን በመረዳት መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታትና የመሪዎች አንድነትን ለመፍጠር የሚያስችል ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ዘመኑ ይርጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!