“በዓለም ባንክ የ58 ሚሊዮን ብር ድጋፍ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች እየተሠሩ ነው” የሸዋሮቢት ከተማ አሥተዳደር

36

ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአካባቢው የሚፈጠሩ ተደጋጋሚ የሰላም እጦቶች በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎች እቅድ አፈጻጸም ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠሩ ስለመኾናቸው የሸዋሮቢት ከተማ አሥተዳደር ከተማና መሰረተ ልማት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ኢሳያስ ዋጋው ተናግረዋል::

ይሁን እንጅ የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎችና ኀብረተሰቡ በተቀናጀ መንገድ በመረባረብ በበጀት ዓመቱ የተያዙ ፕሮጀክቶች ከሰኔ 30 በፊት ሙሉ በሙሉ እንዲጠናቀቁ ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑም አንስተዋል::

በ2015 የበጀት አመት 18 ፕሮጀክቶችን በ58 ሚሊዮን ብር ለማከናወን ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል::

አስሩ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቀዋል። ስምንቱ ከ70 በመቶ እስከ 75 በመቶ ሥራቸው ስለመጠናቀቁም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል::

ሥራ አስኪያጁ ይህን ይበሉ እንጂ ስለ መሰረተ ልማት ግንባታዎቹ አሚኮ ያነጋገራቸው የከተማው ነዋሪዎች በሚሠሩ ግንባታዎች ላይ በፍጥነት ያለመጠናቀቅና የጥራት ችግር ስለመኖሩም አስተያዬታቸውን ሰጥተዋል::

አቶ ኢሳያስ አስተያዬት ሰጪዎቹ ያነሷቸው ችግሮች ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ እንደነበረ ተናግረዋል። በዚህኛው የበጀት ዓመት እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ከዲዛይን ሥራ ጀምሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከር ጠንካራ ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት።

ፕሮጀክቶቹ ኀብረተሰቡን ባሳተፈና የኀብረተሰቡን ጥያቄዎች መነሻ ባደረገ መልኩ እንደሚከናወኑ የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ በየቀበሌው ከኀብረተሰቡ የተውጣጡ ጥራትን የሚከታተሉ ኮሚቴዎች ስለመኖራቸውም ገልጸዋል::

በበጀት ዓመቱ የተያዙት ተግባራትም የጌጠኛ መንገድ ሥራ፣ የማፋሰሻ ቦይ ዝርጋታ፣ የጠጠር መንገድ ሥራና ባለ 15 ክፍል 3 የሥራ እድል መፍጠሪያ ሼድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ስለመኾናቸውም ከጽሕፈት ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል::

በፕሮጀክቶቹ ለ497 ወጣቶች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ እድል መፍጠርም ተችሏል::

ዘጋቢ፡- ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!