በወረባቦ ወረዳ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋ በ11 ቀበሌዎች ያለ ሰብልን ሙሉ በሙሉ ማውደሙን የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ገለጸ፡፡

200

መንጋውን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ቢቀጥልም ተጨማሪ የኬሚካል ርጭት የሚያደርግ አውሮፕላን ያስፈልጋልም ተብሏል፡፡

ባሕር ዳር፡ መስከረም 27/2013ዓ.ም (አብመድ) በምሥራቅ አማራ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋ በተለያዩ አካባቢዎች ጉዳት እያደረሰ ሲሆን በወረባቦ ወረዳ የተከሰተው መንጋ ግን የጉዳት መጠኑ ከፍተኛ መሆኑን የወረዳው አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡

‘‘በተለያዩ ባህላዊ መንገዶች ስንከላከል ቆይተናል’’ ያሉት አርሶ አደሮቹ አሁን ላይ ችግሩ ሙሉ በሙሉ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም፤ የሚመለከተው አካል በተለይ የክልል ግብርና ቢሮና የፌዴራል ግብርና ሚንስቴር ግን የመከላከል ሥራውን በበቂ መጠን እየሠሩ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

በወረባቦ ወረዳ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋ 24 ሺህ ሄክታር የሚሆን መሬት የወረረ መሆኑን የገለጸው የዞኑ ግብርና መምሪያ በበኩሉ ‘‘በወረዳው በ11 ወረዳዎች ይገኝ የነበረ ሰብል ላይ ከ10 እስከ 100 በመቶ ጉዳት አድርሷል’’ ብሏል፡፡

በመንጋውም ከ3 ሺህ 400 በላይ አርሶ አደሮች ሰብላቸው ሙሉ በሙሉና በከፊል እንደወደመባቸው የገለጹት የመምሪያው ኃላፊ ታደሰ ግርማ የበረሃ አንበጣ መንጋውን ለመከላከል ሕዝቡን በማስተባበር እና አሮጌ የመኪና ጎማዎችን ከከተማ በማስመጣት ጪስ እያጨሱ በባህላዊ መንገድ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የመንጋው ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ በመምጣቱ የመከላከል ሥራው ውጤታማ እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡

በስፍራው የበረሃ አንበጣ መንጋ ለመከላከል የኬሚካል ርጭት ስታደርግ የነበረችው ሄሊኮፕተር ከሰሞኑ መከስከሷ መንጋውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ላይ እንቅፋት መፍጠሩንም አመልክተዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥት ተጨማሪ የኬሚካል ርጭት የሚያደርጉ አውሮፕላኖችን ወደ ስፍራው እንዲያሰማራም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የበረሃ አንበጣ መንጋው ያደረሰው ጉዳት በዞኑ ለማምረት የታቀደው ምርት እንዳይገኝ ችግር መፍጠሩንም ተናግረዋል፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ መለስ መኮነን (ዶክተር) ደግሞ የበረሃ አንበጣ መንጋውን ለመከላከል ተጨማሪ አውሮፕላን ከኮምቦልቻ እየተነሳ ርጭት ለማድረግ አስፈላጊ ቁሳቁስ የማቅረብ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፤ ኅብረተሰቡ ሳይዘናጋ አሁንም የመከላከል ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል፡፡

በወረባቦ ወረዳ የአንበጣ መንጋ የተከሰተባቸውን ቀበሌዎች የጉበኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪና የከተማ ልማት ቤቶች ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ሰይድ ኑሩ (ዶክተር) የበረሃ አንበጣ መንጋው ከቆላማ አካባቢዎች ወጥቶ ወደ ደጋማ አካባቢዎች እንዳይዛመት የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አሁን የደረሰው ጉዳት በክልሉ ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ተዕዕኖ የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የግብርና ሚንስትር ድኤታ ወንዳለ ሀብታሙ የበረሃ አንበጣ መንጋውን ለመከለከል ከመጋቢት 2012 ዓ.ም ጀሞሮ እየሠሩ መሆኑን ተናግረው ከምዕራብ የመን፣ ህንድ እና ሰሜን ሶማሊያ የሚነሳ የአንበታ መንጋ የመከለከል ሥራው ላይ መስተጓጎል መፍጠሩንና በተለይ የሎጂስቲክስ አቅማቸውን እየተፈታተነው መምጣቱን ገልፀዋል፡፡ ‘‘ለችግሩ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው’’ ያሉት ሚንስትር ድኤታው የበረሃ አንበጣ መንጋውን ለማሸነፍ ሌሎች ሀገራትም ጭምር እንዲተባበሩ ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡

‘‘ሚንስቴሩ በቻለው መጠን የቅድመ መከላከል ሥራ ሠርቷል’’ ያሉት አቶ ወንዳለ ‘‘ተጨማሪ ግብዓት እያሰባሰብን ነው፤ ፈጥነን በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት እናደርጋለን፤ ኅብረተሰቡም ሊያግዘን ይገባል፡፡ እኛ ብቻችንን ውጤታማ መሆን አንችልም’’ ሲሉም የኅብረተሰቡ የመከላከል ሥራ ሚናው ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አሊ ይመር