በክልሉ የሚሰሩ የመሰረተ ልማት አውታሮች የአካባቢና ማኅበረሰብ ደህንነትን መሰረት ያደረጉ እንዲሆኑ ለማስቻል እየሰራ መሆኑን የአማራ ክልል የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ።

68
ባሕር ዳር:መጋቢት 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በ2014 በጀት ዓመት በከተሞች የተቀናጀ መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም (UIDP) በታቀፍ በምሥራቅ አማራ ዞኖችና ከተሞች የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ተግባራትና የተገኙ የአካባቢ ኦዲት ምርመራ ግኝቶች ላይ የምክክር መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የአማራ ክልል የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ከከተሞች መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር በክልሉ 32 ከተሞች የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ሥራዎች የአካባቢና ማኅበራዊ ደህንነት የአፈፃፀም ኦዲት ምርመራ አድርጓል።
በኦዲት ምርመራው በዓለም ባንክ በጀት በየከተሞቹ የተሰሩ መሰረተ ልማቶች የተገመገሙ ሲሆን ግንባታዎችን በተያዘላቸው ጊዜ ጀምሮ አለማጠናቀቅ እና የጥራት መጓደል በዋነኛነት የሚታዩ ችግሮች መሆናቸውን በባለስልጣኑ የአካባቢ ተቆጣጣሪ እና የከተሞች የተቀናጀ መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም አሥተባባሪ አቶ ጌታቸው ንጋቱ ተናግረዋል።
May be an image of 1 person, standing and outdoors
የኦዲት ግኝቱን ለፈፃሚና ባለድርሻ አካላት በማሳወቅ በክልሉ የመሰረተ ልማት አውታሮች የአካባቢና ማኅበረሰብ ደህንነትን መሰረት ያደረጉ እንዲሆኑ ለማስቻል እየሰራ እንደሚገኝም የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር በልስቲ ፈጠነ ገልጸዋል።
በ2014 በጀት ዓመት የነበሩ ችግሮችን በመፍታት በተያዘው ዓመት የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ጥሩ አፈፃፀም እንዲኖራቸው ለማድረግ ባለድርሻ አካላት በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸው በመድረኩ ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ሀያት መኮነን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!