በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የበረሃ አንበጣ መንጋ መከሰቱ ተገለጸ፡፡

0
169
ባሕር ዳር፡ መስከረም 16/2013ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የበረሃ አንበጣ መንጋ ተከስቷል፡፡ ከአፋር ክልል በመነሳት በባቲ ወረዳ በወዮ ፈላና፣ ጉሬ እና ሰአ መልካ እና ሌሎችም ቀበሌዎች እንደተከሰተ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡
የበረሃ አንበጣ መንጋው ወደ አራት ወረዳዎች ይስፋፋል ተብሎ እየተሰጋ መሆኑንም የብሔረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኃላፊ ኢብሬ ከበደ ለአብመድ አስረድተዋል፡፡ ከአፋር ክልል ጋር በመተባበር የበረሃ አንበጣ መንጋውን እየተከላከሉ እንደሆነም አቶ ኢብሬ ተናግረዋል፡፡
መንጋውን ለመቆጣጠር እንዲቻል የብሔረሰብ አስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች በየወረዳዎች እና የወረዳዎችም ወደ ቀበሌዎች እየተመደቡ እየሠሩ መሆናቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
ባህላዊ በሆነ መንገድ የበረሃ አንበጣ መንጋውን ለመከላከል የቅስቀሳ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አቶ ኢብሬ ጠቁመዋል፡፡ የአጎራባች ክልል ወረዳዎች ማኅበረሰብንም በማሰባሰብ በጋራ የሚከላከሉበት መንገድ እየተመቻቸ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ የጅሌ ጡሙጋ እና አርጡማ ፉርሲ ወረዳዎች ይህን ተግባር ወደ መፈጸም እንደገቡም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
የበረሃ አንበጣ መንጋን በተመለከተ ቅድሚያም ስጋት ስለነበራቸው ኬሚካሎች፣ የመርጫ ቁሳቁስ እና ባለሙያዎችን ሲያዘጋጁ እንደቆዩ የጠቆሙት ኃላፊው “የግብርና ሚኒስቴር የሚመለከታቸውን አካላት በኮምቦልቻ ሰብስቦ የበረሃ አንበጣ መንጋን የመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ከሰጠ በኋላ ማኅበረሰቡንና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ይዘን ወደ ሥራ ገብተናል” ብለዋል::
የበረሃ አንበጣው በባቲ ወረዳ 12 ቀበሌዎችን መውረሩን እና በአፋር ድንበር አካባቢ ሁለት አውሮፕላኖች ርጭት እያደረጉ መሆኑን አቶ ኢብሬ አስረድተዋል፡፡ መንጋው በባህላዊ መንገድም ሆነ በዘመናዊ መንገድ ለመከላከል ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ያስረዱት ኃላፊው ዛሬ መስከረም 16/2013ዓ.ም ተጨማሪ ሁለት አውሮፕላኖች ኮምቦልቻ እንደሚያድሩ እና ነገ መስከረም 17/2013ዓ.ም ወደ ርጭት ዘመቻው እንደሚገቡ ጠቁመዋል፡፡
ከአውሮፕላኖቹ ስምሪት ጎን ለጎን መርጫ የተገጠመላቸው ተሽከርካሪዎችም ሥራ ላይ እየዋሉ እነደሚገኙ ነው አቶ ኢብሬ ያስረዱት፡፡ መንጋው በቁጥጥር ስር እስኪውል ድረስ መላው የአካባቢው ማኅበረሰብ በንቃት እንዲሳተፍም ጠይቀዋል፡፡
አፋር ክልል የተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋ ለብሔረሰብ አስተዳደሩ ብቻ ሳይሆን ለሰሜን ሸዋ፣ ለደቡብ ወሎ ብሎም ለሀገሪቱ የሚያሰጋ እና መጠነ ሰፊ መሆኑን አቶ ኢብሬ አሳስበዋል፡፡ አርሶ አደሩ ከቤተሰቡ ጋር በመሆን የበረሃ አንበጣ መንጋውን ሙሉ ጊዜውን እና ጉልበቱን ተጠቅሞ በባህላዊ መንገድም ጭምር እንዲከላከል፣ ወረርሽኙ በተከሰተ ወቅትም ፈጣን መረጃ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here