በኤሌክትሪክ የብረት ማማዎች ላይ በተፈጸመ ስርቆት የ100 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንዳጋጠመው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለጸ።

72
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ

ባሕር ዳር፤ ታኅሳስ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በ2014 ዓ.ም ብቻ ከኤሌክትሪክ የብረት ማማዎች ላይ በተሰረቀ 756 ቶን ብረት የ100 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንዳጋጠመው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ አስታወቀ፡፡

በዘርፉ የምሥራቅ ሪጅን ዳይሬክተር ጋሻው እንድሪያስ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሚያስተዳድራቸው የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ ተደጋጋሚ ስርቆት እየተፈጸመ ነው፡፡

በ2014 ዓ.ም ብቻ 24 የሚደርሱ ከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊ የብረት ማማዎች ሙሉ ለሙሉ ተቆርጠው ወድቀዋል። የብረትና የኮንዳክተር ዘረፋ ተፈጽሟል። 30 ሺ 257 የሚኾኑ የተለያዩ የታወር ብረቶች በቁማቸው ካሉ ማማዎች ተፈታተው መወሰዳቸውን ተገልጿል፡፡

በ2014 ዓ.ም በስርቆት፣ በመልሶ ግንባታና ከአገልግሎት መቋረጥ ጋር ተያይዞ የባከነውን 2 ሺ 396 ሜጋ ዋት ሰዓት ኃይል ጨምሮ ተቋሙ ከመቶ ሚሊዮን ብር ያላነሰ ኪሳራ እንዳጋጠመው ተናግረዋል፡፡

የተቋሙ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ስርቆትን ለመከላከል ከኅብረተሰብ ተወካዮች፣ ከጸጥታ እና ከፍትሕ አካላት ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶች መካሄዳቸውንና ውጤት እያስገኘ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች በኅብረተሰቡና በባለድርሻ አካላት ትብብር ወንጀሉን ለመከላከል ቢሞከርም በሌሎች አካባቢዎች አሁንም ችግሩ እንደቀጠለ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ተከሰው በሚቀርቡ ወንጀለኞች ላይ የፍትሕ አካላት የሚጥሉት ቅጣት አስተማሪ አለመኾኑና ግብዓት ለማግኘት ሲሉ ስርቆቱን የሚደግፉና የሚረከቡ የብረታብረት ፋብሪካዎችና ባለሀብቶች እንቅስቃሴ ሊፈተሸ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!