በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ በደረሰ ስርቆት እና ጉዳት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ውድመት መድረሱን የክልሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ፡፡

0
252
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 20/2012ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሕዝብ ግኙነት ሥራ አስኪያጅ አቶ ማተቤ ዓለሙ እንዳሉት በ2011 ዓ.ም አገልግሎቱ ካጋጠሙት ችግሮች መካከል ስርቆት እና በመሠረተ ልማት ላይ የሚደርስ ጉዳት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ በክልሉ በሚገኙ ስድት ‹ዲስትሪክቶች› ስር በሚገኙ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት የመሠረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ስርቆትና ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላ በ2011 በጀት ዓመት በአማራ ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ላይ 10 ሚሊዮን 537 ሺህ 852 ብር የሚገመት ስርቆት እና ጉዳት ደርሷል፡፡
 
አቶ ማተቤ እንዳሉት በባሕር ዳር ዲስትሪክት በደረሰ ስርቆት 1 ሚሊዮን 479 ሺህ ብር የሚደርስ ጉዳት ደርሷል፡፡ በዚህ የተነሳም በባሕር ዳር ከተማ አብዛኛው የመንገድ መብራት አገልግሎት አይሰጥም፡፡ የዚህ መሠረታዊ ችግር ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የመንገድ መብራት ሳጥን (ቦክስ) መከፈት፣ የፊውዝ፣ የትራንስፈርመር፣ የአልሙኒዬም ሽቦ እና ሌሎች የመብራት መሠረተ ልማቶች ስርቆት መሆኑን አቶ ማተቤ ተናግረዋል፡፡ በዲስትሪክቱ ወረታ እና አዴት የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትም ተመሳሳይ የስርቆት እና የውድመት ችግሮች ደርሰዋል፡፡
 
በ2012 ዓ.ም ከባሕር ዳር ወደ አዴት ከተዘረጋው መስመር ላይ ሽቦ ለመስረቅ ሲባል የኤሌክትሪክ መስመር ተቆርጧል፤ 710 ሜትር ሽቦም ባልታወቁ ሰዎች ተቆርጦ ተወስዷል፡፡ ከጢስ ዓባይ ባሕር ዳር ቁጥር አንድ አገልግሎት መስጫ ማዕከል 45 ኪሎ ቮልት ማስተላለፊያ መስመር የታወር ብሎን ባልታወቁ ሰዎች በመፈታቱ ከባሕር ዳር ወደ አዴት በተዘረጋው የኤሌትሪክ ሽቦ ላይ ወድቆ የአዴት ጎንጂ ደንበኞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዳያገኙ ተደርገዋል፡፡
 
በደብረ ማርቆስ፣ ደሴ፣ ጎንደር፣ ወልድያ፣ ደብረ ብርሃን ዲስትሪክት አገልግሎት መስጫ ማዕከላትም ተመሳሳይ ጉዳት ደርሷል፡፡ ስርቆቱም ተቋሙ ከኤሌትሪክ ሽያጭ ማግኘት የሚገባውን ገቢ እንዲያጣ አድርጎታል፣ የሀገሪቱን ሀብትም አባክኗል፡፡ በዋናነት ደግሞ በአገልግሎቱ ደንበኞች ላይ በገንዘብ ሊተመን የማይችል ከባድ ኪሳራ ደርሷል፡፡
 
የኢነርጂ አዋጅ 810/2006 አንቀጽ 26 በኃይል ማመንጫ፣ ማስተላለፊያ ወይም ማከፋፈያ ተቋማት ላይ ጉዳት ያደረሰ ማንኛውም ሰው ከ5 እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ወይም እስከ 50 ሺህ ብር በሚደርስ ገንዘብ ወይም በሁለቱም እንደሚቀጣ አስቀምጧል፡፡ በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 29 ላይ በኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ ማናቸውንም ኤሌክትሪክ አስተላላፊ ነገር ያስቀመጠ፣ የኤሌክትሪክ እቃ ያስቀመጠ፣ የተከለ፣ የዘረጋ ወይም እንዲተከል እንዲዘረጋ የፈቀደ፣ በኤሌክትሪክ ‹ኢንስታሌሽን› ይዞታ ውስጥ ግንባታ የሚያከናውን፣ የሚያርስ ወይም የሚቆፍር፣ በኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ወይም የሚያውኩ ግንባታዎችን አላፈርስም፣ ዛፎችን አልቆርጥም ወይም አልመለምልም፣ ሰብሎችን፣ አትክልቶችን ወይም ሌሎች ነገሮችን አላስወግድም ያለ እንደሆነ፤ ማናቸውም የኤሌክትሪክ መስመር ተሸካሚ አካላትን ያለያየ፣ የሰረቀ ወይም በማለያየትና በስርቆት የተባበረ እንደሆነ፣ በኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ ሆን ብሎ ወይም በግዴለሽነት ጉዳት በማድረስ ያቋረጠ እንደሆነ፣ እስከ 5 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ወይም ከብር 25 ሺህ ባልበለጠ የገንዘብ መቀጮ ወይም በሁለቱም እንደሚቀጣ ያስቀምጣል፡፡
 
የክልሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰሎሞን ጣሰው ምንም እንኳን በቂ ሕግ ቢቀመጥም ተግባራዊነቱ ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሕጉን በአግባቡ የመረዳት ችግር በመኖሩ ዘረፋ እና ውድመት መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ ሌላ ተልዕኮ ያላቸው አካላትም ባለፉት ሁለት ዓመታት የተፈጠረውን ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ጥፋቱን ፈጽመዋል፡፡ ጥፋት ሲፈጽሙ በተገኙ አካላት ላይ የእስራት፣ የገንዘብ እና የጠፋውን ንብረት የማስመለስ ሥራዎች መከናዎናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ከደረሰው ጉዳት አንጻር አጥፊዎችን በትክክል ተከታትሎ ለሕግ የማቅርብ ችግር መኖሩንም አመላክተዋል፡፡
ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመከላከል በስውር ጥፋት የሚፈጽሙ አካላትን በማጋለጥና መሠረተ ልማትን በመጠበቅ ኅብረተሰቡ ተባባሪ ሊሆን እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡ በየደረጃው ያለ ሕግ አስከባሪ አካላትም ጥፋተኞችን ለሕግ በማቅረብ መሠረተ ልማቱን ከጥፋት መታደግ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
 
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ