በኢትዮጵያ 30 ተጨማሪ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው፤ 14 ተጨማሪ ሰዎች ደግሞ አገገሙ፡፡

0
136

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 19/2012 ዓ.ም (አብመድ) በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት ለ4 ሺህ 352 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ በ30 ሰዎች ላይ የኮሮና ቫይረስ ተገኝቷል፡፡ ቫይረሱ ከተገኘባቸው መካከል 14 ሰዎች የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክም ሆነ አስቀድሞ ቫይረሱ እንዳለበት በሕክምና ከተረጋገጠ ሰው ጋር ንክኪ የሌላቸው ናቸው፡፡

እንደጤና ሚኒስቴር መረጃ አዲስ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል አስራ አንዱ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ አላቸው፤ አምስቱ ደግሞ አስቀድሞ በቫይረሱ መያዛቸው በሕክምና ከተረጋገጡ ሰዎች ጋር ንክኪ አላቸው፡፡

ዛሬ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ከተረጋገጡት መካከል 15 ከአዲስ አበባ ሲሆኑ አስቀድሞ በቫይረሱ መያዙ በሕክምና ምርመራ ከተረጋገጠ ሰው ጋር ንክኪ ነበራቸው፡፡ ሁለቱ ከትግራይ ክልል ሆነው የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያላቸውና በለይቶ ማቆያ ያሉ ናቸው፡፡ ከአማራ ክልል ደግሞ ስምንት ሰዎች ላይ ቫይረሱ ተገኝቷል፤ ሁሉም የውጭ ሀገር ጉዞ ያላቸውና በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ ናቸው፡፡

አንድ የጉዞ ታሪክም ሆነ አስቀድሞ በቫይረሱ መያዙ በሕክምና ከተረጋገጠ ሰው ንክኪ የሌላቸው ሰው ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡ ከሐረሪ ክልል ደግሞ ሦስት ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፤ ሁሉም አስቀድሞ በቫይረሱ መያዙ በሕክምና ምርመራ ከተረጋገጠ ሰው ጋር ንክኪ ነበራቸው፡፡ አንድ የድንበር ተሻጋሪ መኪና አሽከርካሪም ቫይረሱ ከተገኘባቸው መካከል ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ እስከዛሬ 91 ሺህ 616 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው በ731 ላይ ቫይረሱ መገኘቱ ተረጋግጧል፤ የዛሬዎቹን 14 ሰዎችን ጨምሮ 181 ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል፡፡ በበሽታው ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ስድስት ደርሷል፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡