አቶ ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ: የካቲት 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ውስጥ በዘመናት እና በአሁኑ ጊዜ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የሽግግር ፍትሕን መተግበር አስፈላጊ መኾኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡
አቶ ደመቀ ይህንን ያሉት በብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አማራጮች ላይ የሚካሄድ የግብዓት መድረክ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
መድረኩ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ባካተተ መልኩ የተሟላ ሀገራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊስ ትግበራን ማምጣት ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል።
የፍትሕ ሚኒስቴር ባዘጋጀው በዚህ መድረክ የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮች፣ የምክር ቤት አፈጉባኤዎች ፣ሚኒስትሮች፣ የሕግ ማኀበራት ተወካዮች፣ የሃይማኖት አባቶችና የዓለም አቀፍ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ችግሮቻችን በጋራ እየፈታን የተከበረች ሀገር ገንብተን ረዥም መንገድ ተጉዘናል፤ አሁን ላይ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመፍታት በሰለጠነ መንገድ መነጋገር ቀዳሚ መፍትሔ ሊኾን ይገባል ነው ያሉት።
የመንግሥት ኀላፊነት ሕግ ማስከበር፣ የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ማክበር እና ተጠያቂነትን ማምጣት ነው። ይሁን እና በዚህ አጋጣሚ በተፈጠሩ ችግሮች የበዳይ ተበዳይ ትርክቶች ተፈጥረው ቆይተዋል። ችግሮቹ በአፋጣኝ ባለመፈታታቸው እና ፍትሕ ባለማግኘታቸው ለአዳዲስ ግጭቶች ምንጭ እየኾኑ መጥተዋል። እነዚህን እና ለረዥም ጊዜ የመጡ ችግሮችን ለመፍታት የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊ ኾኗል። ይህ የሽግግር ሥርዓት እውነትን ፣ተጠያቂነትን እና ይቅር መባባልን መዳረሻው ማድረግ አለበት። ይህ እንዲሳካ ሁሉም የበኩልን ማድረግ አለበት ብለዋል።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!