በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል የሚስተዋለውን የድንበር ውዝግብን ለመፍታት የሀገራቱ ታሪካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ብቻውን በቂ መሆኑን ምሁራን ገለፁ፡፡

0
90
በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል የሚስተዋለውን የድንበር ውዝግብን ለመፍታት የሀገራቱ ታሪካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ብቻውን በቂ መሆኑን ምሁራን ገለፁ፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 04/2013 ዓ.ም (አብመድ) በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል የሚስተዋለውን የድንበር ውዝግብ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል እና አማራጮችን የሚያመላክት ውይይት በሁለቱ ሀገራት ምሁራን ተጀምሯል፡፡ በውይይቱ ሀገራቱ የነበሯቸው ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማህበራዊ ትስስሮች መቅረባቸው ለችግሩ ዘላቂ እና ጊዜያዊ መፍትሄ አማራጮች እንዲሆኑ ይረዳል ተብሏል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል የድንበር ውዝግብ ተስተውሏል ያሉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር እና የውይይቱ አስተባባሪ ሞገስ አብርሃ ውይይቱ ለድንበር አካባቢ ውዝግቡ ዘላቂ መፍትሄ እስኪበጅለት ድረስ ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ሰላም ታሪካዊ እርሾዎችን ማውሳት ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከገዳሪፍ ዩኒቨርሲቲ እና ከሱዳን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የጠበቀ የእርስ በእርስ ግንኙነት መኖሩን አውስተው ያንን አጠናክሮ ማስቀጠል ለሁለቱ ሀገራት ሰላማዊ ግንኙነት አጋዥ ይሆናል ነው ያሉት፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ቃለወንጌል ምናለ (ዶክተር) በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረው የድንበር ውዝግብ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን እንዳያውከው የኀይል አማራጮችን ዝግ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
የድንበር ውዝግቡ በሁለቱ ሀገራት መንግስታት ብቻ መፈታት ይኖርበታል ያሉት ዶክተር ቃለወንጌል ሁለቱ ሀገራት ከሀገረ መንግስት ግንባታ ጀምሮ ያላቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እና ትስስር ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ብቻውን በቂ ነው ብለዋል፡፡
የድንበር ውዝግቡ ሱዳን የገጠማትን ወቅታዊ የውስጥ ችግር ለማስታገስ ስትል የፈጠረችው አጀንዳ ሊሆን ይችላል? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ዶክተር ቃለወንጌል ይህን መሰል አካሄዶች በአፍሪካ ሃገራት በተደጋጋሚ እንደሚያጋጥሙ ጠቅሰው ኢትዮጵያ ግን የውስጥ አንድነቷን አጠናክራ ጉዳዩን በህግ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ጥረቷን መቀጠል ይኖርባታል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here