በኢትዮጵያ ሦስት ተጨማሪ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው፡፡

0
175

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 11/2012 ዓ.ም (አብመድ) በኢትዮጵያ ሦስት ተጨማሪ ሰዎች ላይ የኮሮና ቫይረስ መገኘቱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ሚኒስቴሩ በማኅበራዊ ገጹ እንዳመለከተው ባለፉት 24 ሰዓታት ለ667 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ በሦስት ሰዎች ላይ ቫይረሱ ተገኝቷል፡፡

ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች ሁለቱ ከውጭ የገቡና በለይቶ ማቆያ የነበሩ መሆኑ ተመላክቷል፤ አንዷ የጉዞ ታሪክ የሌላቸው የአዲስ አበባ ነዋሪ መሆናቸውና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ የነበራቸው ስለመሆኑ እየተጣራ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ እስከዛሬ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች ቁጥር 7 ሺህ 557 ደርሷል፤ ቫይረሱ የተገኘባቸው ደግሞ 108 ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 16 ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል፤ 3 ሕይወታቸው አልፏል፤ በሕክምና ላይ የሚገኙት 87 ሲሆኑ አንድ ታካሚ በጽኑ ሕሙማን ክፍል ይገኛሉ፡፡