“በኢትዮጵያ መፃኢ እድል ፈንታ ከቶውንም አንሸሽም፤ አንደራደርም” ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ

0
62
“በኢትዮጵያ መፃኢ እድል ፈንታ ከቶውንም አንሸሽም፤ አንደራደርም” ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች በደብረ ታቦር ከተማ የድጋፍ ሰልፍና የምርጫ ቅስቀሳ አድርገዋል። በምርጫ የድጋፍ ሰልፉ የተገኙት የኢፌዴሪ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትሯና የአካባቢው እጩ ተወዳዳሪ ሂሩት ካሳው (ዶክተር) መክሮና ገስፆ ያሳደገን ኩሩ ሕዝብን መወከል ኩራት ነው ብለዋል።
ባለ ታሪክ፣ ኩሩና ደፋር ሕዝብ ሀገር መምራት እንደሚቻልና ለዓላማ ፅኑ መሆን አስተምሯልም ብለዋል ሚኒስትሯ። እቴጌ ጣይቱን ያፈለቀው አካባቢ ዛሬም ድረስ ጀግኖችና ጠቢባንን እያፈለቀ ስለመሆኑም ተናግረዋል። ደብረታቦር ለኢትዮጵያ ምሰሶ ሆና ታላቅ ታሪክ እንደተሠራባት ሁሉ ዛሬም ሆነ ወደፊት እንደ ስሟ ከፍ ያለ ተራራ ሆና ደምቃ መታዬት ይኖርባታል ብለዋል። የቀደሙት ነገሥታት፣ መኳንንትና መሳፍንት ደብረ ታቦርን የመንግሥታቸው መንበር ሲያደርጉ የብልሆች ቦታ መሆኗን አስተውለው እንደነበር ዶክተር ሂሩት አንስተዋል፡፡
ዶክተር ሂሩት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የሕዝብ አመራርን መልክ ያስያዙበትና ኢትዮጵያን አንድ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የጥበብ ማእከል እንድትሆን ጋፋት ላይ ኢንዱስትሪ ዘርግተው እንደነበር ጠቅሰዋል። ታላቁ መሪ ቴዎድሮስ ጋፋት ላይ ሥራቸውን ሲጀምሩ የቦታውን ምቹነት፣ የማኅበረሰቡን ጥበብና ብልሃት በሚገባ ተረደተው ነው፤ ዓላማቸውም ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ማማ መውሰድና ታላቅ ሀገር ማድረግ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ “የእነዚያ ጥበበኛ ልጆች ዛሬም በብሩኩ ምድር ያለን በመሆኑ የሩቅ አሳቢውን የልማት ዓርማ አንስተን አካባቢያችንን የልማት ማእከል በማድረግ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ማማ እናወጣታለን” ብለዋል።
ዶክተር ሂሩት ጥበብን ከጀግንነት ጋር የያዘውን ማኅበረሰብ በአንድነት እንዲቆም በማድረግ ኢትዮጵያ ከፍ ወደ አለ ደረጃ እንድትራመድ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።
የጣይቱ ምክርና ጀግንነት በኢትዮጵያ ብሎም በጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ያመጣውን ገድል ያስታወሱት ዶክተር ሂሩት እድል ከተሰጣቸው የዘመኑ አርበኞች ለመሆን እንደሚሠሩም አስታውቀዋል። ድምፅ አግኝተው ከተመረጡ የጋፋት ጥበብ ዳግም እንዲያብብና አካባቢው ወደ ሁለንተናዊ ከፍታ እንዲራመድ እንደሚሠሩም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የምትለወጥበትን ሥራ እንደሚሠሩም ተናግረዋል። በደብረ ታቦርና አካባቢው የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ፣ የልማትና የጥበብ ማእከል በመሆኑ የቀደመው ስሙንና አሁንም ያለውን የመልማት አቅም አስጠብቆ እንዲቀጥል እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእስ መሥተዳድር ፈንታ ማንደፍሮ (ዶክተር) የአማራ ሕዝብ ኢትዮጵያን ማንሳት ብቻ ሳይሆን ስለ ኢትዮጵያ መሞት የታሪኩ አካል ብቻ ሳይሆን አምድ ነው ብለዋል።
ምክትል ርእስ መሥተዳድሩ እንዳሉት ኢትዮጵያ በርካቶች በቅኝ ግዛት ባርነት በወደቁበት ጊዜ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ከዛፍ ላይ እንደተሰቀለ መብራት ከርቀት አብርታ የታዬች ምልክት ሀገር ናት፤ ኢትዮጵያ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ነፃ መሆን እንደሚገባቸው ያስተማረች፣ ያሰለጠነች፣ ነፃም እንዲወጡ የታገለች ታላቅ ሀገር ናት፤“ አባቶች በዚያ ዘመን በታላቅ ተጋድሎ ነፃ ያደረጓትን ሀገር ዓለም ነፃ በወጣበት ጊዜ የነፃነት አርማዋ እንዲደበዝዝ ሲፈለግ ልጇቿ እንዴት ዝም እንላለን?” ሲሉም ጠይቀዋል።
“የማይሸሽ ሕዝብ ልጆች ነንና በኢትዮጵያ መፃኢ እድል ፈንታ ከቶውንም አንሸሽም፤ አንደራደርም፤ ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ የእነ አፄ ቴዎድሮስ ልጆች ነንና ለስልጣን ሳይሆን ለሀገር እንጓጓለን” ብለዋል ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ።
ዶክተር ፈንታ የውስጡም ሆነ የውጭ ጠላት ያላወቀው ነገር ኢትዮጵያውያን ለነፃነታቸው ቀናዒ የሆኑና የሕይወት ዋጋ ለመክፈል የማይሳሱ መሆናቸውን ነው ብለዋል። ከዘመን በፊት ነፃ የሆነች ሀገር በቀኝ ግዛት ያልተገዛች ሀገር የሚለው ታሪክ የሚያማቸው ኃይሎች ቢኖሩም አይሳካም፣ ኢትዮጵያ አትደፈርም ብለዋል።
በኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ ውስጥ የአማራ ሕዝብ ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን አይተኬ ሚና መጫወቱን ራሱ ሳይሆን ሌሎች ኢትዮጵያውያን እንደሚመሰክሩም ገልጸዋል።
ዶክተር ፈንታ “ብልጽግና የደም ዋጋ የተከፈለበት ነው፣ የኢትዮጵያን እና የአማራን ሕዝብ ጥቅም አሳልፎ የሚደራደር ፓርቲ አይደለም፤ ከማንም ጋር አይጎብጥም” ብለዋል። ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ወንበር የመለዋወጥ ጉዳይ ሳይሆን ኢትዮጵያን የማስቀጠልና ያለ ማስቀጠል ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል። ብልጽግና በኢትዮጵያ ላይ የተሸረቡትን ሴራዎች የሚያፈርስ ስለመሆኑም ተናግረዋል። ኢትዮጵያን በነፃነቷ ተከብራ ለማስቀጠል ምርጫው ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል።
ዶክተር ፈንታ እንደገለጹት ደብረ ታቦር ከተማ እድሜዋን ሳይሆን ከእድሜዋ እየተቀነሰ የኖረች ከተማ ናት፤ የደብረ ታቦር ሕዝብ በበቀል የደኸየ ነው። ደብረ ታቦር ወደ ሪጅዮ ፓሊታንት እንድታድግ የተነሳው ጥያቄ እየታየ መሆኑን ዶክተር ፈንታ አስታውቀዋል። ከተማዋ እንድትበለጽግ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here