በአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ የሚኖሩ የአማራ ተወላጅ ነጋዴዎች ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለልዩ ኃይል፣ ለሚሊሻና ፋኖ የምግብና አልባሳት ድጋፍ አደረጉ፡፡

0
103

ባሕር ዳር፡ ጳጉሜን 01/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ የሚኖሩ የአማራ ተወላጅ ነጋዴዎች 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበትን ምግብና አልባሳት ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለልዩ ኃይል፣ ለሚሊሻና ለፋኖ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

የድጋፉ አስተባባሪ አቶ ዓለሙ ዘውዴ እንደገለጹት በአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማና በሌሎችም ክፍለ ከተሞች የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ሀገርን ከጥፋት ለመታደግ እየተፋለመ ለሚገኘው የወገን ጦር በአጭር ጊዜ በተሰበሰበው የ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ምግብና አልባሳት በመግዛት ድጋፍ ተደርጓል፡፡

አቶ ዓለሙ ነጋዴዎቹ የሀገርን ሉዓላዊነት ለመታደግ እየተፋለመ ካለው የጸጥታ ኀይል ጎን መቆማቸውን አስታውቀዋል፡፡ ሌሎችም መሰል ድጋፎችን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከዚህ በፊትም ገንዘብ በመሰብሰብ በሕጋዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴው የባንክ ሒሳብ ቁጥር ማስገባታቸውን የገለጹት አስተባባሪው በቀጣይም የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ዓለሙ አረጋግጠዋል፡፡

ድጋፉን የተረከቡት የአማራ ልዩ ኃይል ሎጀስቲክስ አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ዘውዱ እሸቴ ደጀን የሆነው ሕዝብ እያደረገ የሚገኘው ድጋፍ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ የተሰጠውን ግዳጅ በአግባቡ እንዲወጣ የሞራል ስንቅ እንደሆነው ተናግረዋል፡፡

“በጋራ ስንቆም የማንወጣው ችግር የለም” ያሉት ሜጄር ጄኔራሉ ሕዝቡ ከጸጥታ አካሉ ጎን በመቆም የተጋረጠውን የህልውና አደጋ በጋራ እየመከተ ነው ብለዋል፡፡ ዛሬ በአዲስ አባባ ከተማ ከሚኖሩ ነጋዴዎች ለተደረገው ድጋፍም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የሚኖሩ ሁሉም ዜጎች የህልውና ዘመቻው በድል እስከሚጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m