በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የአማራ ክልል ምክር ቤት አቅጣጫ አስቀመጠ።

0
75

ባሕር ዳር፡ ጥር 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴዎች አባላት በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወረራ የወደሙና የተዘረፉ አካባቢዎችን የመስክ ምልከታ አድርገዋል። ቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ምልከታቸዉን መሰረት በማድረግ ከክልሉ የቢሮ ኀላፊዎች ጋር የወደሙ ተቋማትን መልሶ ወደ ሥራ ማስገባት ሂደትን በተመለከተ መክረዋል።

በአማራ ክልል ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ዓለም ዋጋዬ ቋሚ ኮሚቴዎቹ የተመለከቱትን ጉዳቶች ለአስፈፃሚዎች ሪፖርት አቅርበዋል። ቋሚ ኮሚቴዎቹ የሽብር ቡድኑ ወረራ ፈጽሞ ከነበረባቸው አካባቢዎች ውስጥ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ደቡብ ጎንደርና ሰሜን ሸዋ ዞኖችን፣ ደሴ ከተማ አስተዳደርን እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደርን መመልከታቸውን ነው የጠቆሙት፤ ወይዘሮ ዓለም አሁን በፍጥነት አስፈፃሚዎቹ ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡ በቀጣይ ሰሜን ጎንደርንና ዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደርን እንደሚመለከቱም ጠቁመዋል።

ወይዘሮ ዓለም ቋሚ ኮሚቴዎቹ በሽብር ቡድኑ የሕዝብ፣ የግለሰቦች፣ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ላይ ያደረሰውን መጠነ ሠፊ ዘረፋና ውድመት የሚያመላክት ሪፖርት በዝርዝር አቅርበዋል። አሸባሪው ቡድኑ ከግድያ፣ ሴቶችና አረጋውያንን ከመድፈር፣ ከዘረፋና ውድመት በተጨማሪ የሕዝብን እሴት ሲያንቋሽሽ እንደነበረም አመላክተዋል። የሽብር ቡድኑ መንግሥትና ሕዝብን ለማለያየት ሰነዶችን አውድሟል፤ አጥፍቷል ብለዋል። በጤና ተቋማት ላይ ሰነዶችን በማጥፋት የታካሚዎች ታሪክ እንዳይታወቅ አድርጓልም ነው ያሉት።

ቋሚ ኮሚቴዎቹ የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍ እና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ለመጠገን የሚደረገውን ጥረት መመልከታቸውን ወይዘሮ ዓለም ባቀረቡት ሪፖርት ጠቁመዋል። በወረራ ስር የነበረው ሕዝብ መድኃኒት ሳይቀር ሲካፈል እንደነበር እና የሃይማኖት አባቶች ሕዝቡን በመደገፍ ያሳለፉትን የችግር ወቅት አድንቀዋል። በተለይ ኅብረተሰቡ ከፍርሃት ወጥቶ ወደ መደበኛ ሥራው እንዲገባ፣ የጠላትን ሁኔታ አይቶ ብቻ ሳይሆን ሁሌ ራሱን በማደራጀት አካባቢውን እንዲጠብቅ፣ የሚሰበሰቡ ድጋፎች በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውሉ፣ የመንግሥት ሠራተኞች ማነቃቂያ እንዲደረግላቸው ቋሚ ኮሚቴዎቹ ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል። ሁሉም ቢሮዎች የመልሶ መገንባት እቅድ ይዘው ሊሠሩ እንደሚገባ ወይዘሮ ዓለም ባቀረቡት ሪፖርት አሳስበዋል።

የቀረበውን ሪፖርት በመከታተል የክልሉ አስፈፃሚዎች በሰጡት ሀሳብ ወቅቱ የፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም የመንግሥት ተቋማት ከሙስና የጸዳ፣ ታማኝ፣ ቅንና ፈጣን አገልግሎት ለሕዝብ መስጠት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። በወረዳ የሚገኙ ምክር ቤቶች ሕዝቡ ፈጣን አገልግሎት ሊያገኝ በሚችልበት ሁኔታ ላይ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል። ሴቶችና ሕፃናት ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመጠገን ተቋማት ቅንጅታዊ ሥራ መሥራት አለባቸው ብለዋል። ተጎጂዎች የሥነልቦና ጥገና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም ጠቁመዋል።

ሥራ አስፈጻሚዎቹ ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ራሳቸውን እስኪችሉ በቂ የምግብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋልም ብለዋል። መምሕራንና የሥራ ኀላፊዎች ከሥነ ልቦና ጉዳት ወጥተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ስልጠና ተሰጥቷል፤ የትምሕርት ተቋማት መውደማቸው ብቻ ሳይሆን ጠላት የጅምላ መቅበሪያ ቦታም እንዳደረገው አስፈፃሚዎቹ ተናግረዋል። አፈርና ድንጋይ ላይም ቢሆን ተቀምጠው ትምሕርት የጀመሩ አካባቢዎች መኖራቸውን አስረድተዋል። በወረራ ሥር የነበሩ ዜጎችን መቅረብ፣ ማረጋጋትና መደገፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በውይይቱ ላይ በወረራ ስር ለነበሩ 11 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች በወር ቢያንስ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል እህል ያስፈልጋልም ተብሏል። ለተጎጂዎቹ በየወሩ የምግብ እህል እየቀረበ እንደሚገኝና ለተደራሽነቱና ለፍትሐዊነቱ እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል።

ሥራ አስፈጻሚዎቹ የሽብር ቡድኑ ሰነዶችን ያወደመው የአማራ ሕዝብ ሰነድን ለማፈላለግ ጊዜውን እንዲያጠፋ በመፈለግ ነው ብለዋል። ኅብረተሰቡ እንዲረጋጋ መደበኛ ሕይወቱን እንዲቀጥል የመንግሥት ተቋማት ሥራ መጀመር እንዳለባቸው አስፈፃሚዎቹ ተናግረዋል። የጉዳት መጠኑና ዓይነቱን በመለየት በመልሶ ጥገናው ላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባልም ብለዋል።
ለወደፊት የመንግሥት ተቋማት መረጃዎችን ዲጂታል ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል። ሕዝቡን የውሳኔ አካል በማድረግ የተጋረጡ ችግሮችን መፍታት፣ ኅብረተሰቡ በራሱ የሚረዳዳበትን መንገድ መቀየስ ተገቢ እንደሆነም ተነስቷል።

የሥራ ኀላፊዎች ሕዝብንና መንግሥትን የሚያቀራርብ ሥራዎችን መሥራት እንዳለባቸው የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ አሳስበዋል። ቋሚ ኮሚቴው አስፈፃሚዎች እቅዳቸውን ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች በማውረድ የሚተገብሩትን ተግባራት እንደሚከታተል ገልጸዋል። “ሕዝቡ ቆጥሮ የሰጠንን ሥራ በተግባር ማሳየት አለብን” ነው ያሉት። አፈ ጉባዔዋ እንዳሉት ሁሉም ሥራዎች በመረጃ ላይ የተደገፉ መኾን አለባቸው። ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሁሉም መሥሪያቤቶች ኅብረተሰቡን ለማገልገል ያደረጉትን ጥረት ወይዘሮ ፋንቱ አድንቀዋል። የወደሙና የተዘረፉ መሰረተ ልማቶችን ለመጠገን መሥሪያቤቶች በቅንጅት መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/