በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በምሥራቅ አማራ እና በአፋር የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ የተጎዱ የፋይበር ኦፒቲክስ መስመሮች ጥገና እየተከናወነ ነው፡፡

0
82

መጋቢት 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፋይበር ኦፕቲክስ የኦፕሬሽንና ጥገና ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ ገብረ መድህን እንደተናገሩት በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ከኮምቦልቻ- ሰመራ፣ ከሸዋሮቢት – ኮምቦልቻ እንዲሁም ከኮምቦልቻ- አቀስታ ከኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ምሦሦዎች አናት ላይ ተዘርግተው በሚገኙ የፋይበር ኦፕቲክስ መስመሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

የፋይበር ኦፕቲክስ መስመሮቹ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች መከላከያ ከመስጠት ባለፈ ለቴሌ ኮሙኒኬሽን ሥራዎች እና ከኃይል ማመንጫ እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች መረጃዎችን ወደ ብሔራዊ ኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል ለማድረስ እንደሚያግዙ አቶ ኤርሚያስ አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ መስመሮቹ በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት የብሔራዊ ኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከሉ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ያሉ መረጃዎችን መሰብሰብና መመልከት አለመቻሉን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ጉዳት በደረሰባቸው መስመሮች ላይ የፋይበር ኦፕቲክስ ተከራይቶ ይጠቀም እንደነበር ያስታወሱት አቶ ኤርሚያስ በደረሰው ጉዳት ምክንያትም አገልግሎቱ ተቋርጦ ቆይቷል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸውን መስመሮች በመጠገን ወደ አገልግሎት ለማስገባት እየተሠራ እንደኾነም ሥራ አስኪያጁ አንስተዋል፡፡

የፋይበር ኦፕቲክስ የጥገና ሥራ ጥንቃቄን የሚጠይቅና አድካሚ እንደኾነ ያነሱት አቶ ኤርሚያስ አገልግሎቱን ለኅብረተሰቡ በወቅቱ ለማድረስ ሁሉም ሠራተኛ በከፍተኛ ተነሳሽነት፣ በመተሳሰብና በመደጋገፍ የጥገና ሥራውን እያከናወነ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ጉዳት የደረሰባቸውን የፋይበር ኦፕቲክስ መስመሮች ለመለየት የሚከናወነው ሥራ ከጥገና ሥራው የማይተናነስ አድካሚና አስቸጋሪ በመሆኑ ‘‘OTDR (Optical Time Domain Reflector’’ በተሰኘ ማሽን በመታገዝ ጉዳቱን በመለየት የጥገና ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

በአካባቢው ያለው ኅብረተሰብ የኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘው ከረጅም ጊዜ በኋላ በመኾኑና ለጥገና ሥራ በሚል ኤሌክትሪክ በተከታታይ እንዳይቋረጥበት በማሰብ በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ኤሌክትሪክ በማቋረጥ ጥገናው እየተከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

ከኮምቦልቻ- ሰመራ በተዘረጋው የፋይበር ኦፕቲክስ መስመር ላይ ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ በሚኾነው ላይ ጉዳት የደረሰበት ቢኾንም ኹሉንም በአዲስ በመቀየር ደሴ ከተማ ከሚገኘው የኢትዮ ቴሌኮም ሰርቨር ጋር ማገናኘት ተችሏል ብለዋል፡፡

ከሸዋ ሮቢት – ኮምቦልቻ በተዘረጋው የፋይበር ኦፕቲክስ መስመር ላይ ደግሞ 33 ኪሎ ሜትር በሚኾነው ላይ ጉዳት የደረሰ ሲኾን ከዚህ ውስጥ 18 ኪሎ ሜትር የሚኾነውን በአዲስ መቀየር መቻሉን ነው የጠቆሙት፡፡ የ15 ኪሎ ሜትሩን ቀሪ ሥራዎች በቀጣዮቹ ኹለት ሳምንታት በሚገኙት እሁድ ቀናት ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደሚሠራ መግለጻቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡

ከኮምቦልቻ- አቀስታ ባለው የፋይበር ኦፕቲክስ መስመር ላይ ጉዳት እንደደረሰበትም ታውቋል፡፡

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/