“በአሸባሪው ቡድን በደረሰው መጠነ ሰፊ ውድመትና ዝርፊያ የተጎዳውን ሕዝባችን ለማቋቋም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ርብርብ ያስፈልጋል” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

0
118

“በአሸባሪው ቡድን በደረሰው መጠነ ሰፊ ውድመትና ዝርፊያ የተጎዳውን ሕዝባችን ለማቋቋም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ርብርብ ያስፈልጋል” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ
ታኅሣሥ 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በአማራ ክልል በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ምክንያት የደረሰውን መጠነ ሰፊ ውድመትና ዝርፊያ በማጥናት መልሶ ለመገንባትና የተጎዳውን ሕዝባችን ለማቋቋም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የተፈናቀሉ ዜጎችን በፍጥነት ወደ ነበሩበት ቀየ መመለስና የሚያስፈልጋቸውን መሰረታዊ አገልግሎቶችና የሰብዓዊ እርዳታ ሳይውል ሳያድር በፍጥነት ማቅረብ ጊዜ የማይሰጠው አንገብጋቢ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
“የመልሶ ግንባታና ማቋቋም ሥራችንን አጣዳፊነት ያክል በትክክለኛ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ ውጤታማ ሥራ ለመሥራትም ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ግድ ይለናል፡፡ በመሆኑም ክልላዊ የመልሶ ግንባታና ማቋቋም ኮሚቴ ተቋቁሞ የደረሰውን የጉዳት መጠን የማጥናት ሥራ የጀመረ ሲሆን በተጨባጭ መሬት ላይ ያለውን እውነታና የጥናቱን ውጤት ለሕዝባችን የምናሳውቅ ይሆናል” ነው ያሉት፡፡
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ለመመከት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተረባረበውን ያክል አሁንም ይህ አሸባሪ ቡድን ያደረሰውን ጉዳት በኢትዮጵያውያን ርብርብ ማከምና መጠገን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ በሕዝብ ላይ ያደረሰውን መጠነ ሰፊ ጉዳት ለማከም ሁሉም ኢትዮጵያውያን ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን የዜግነት ግዴታ መወጣት ይገባል፤ የተጀመረውን የድጋፍ አሰባሰብ ሥራም አጠናክሮ ማስቀጠል የሁሉም ተግባር እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡
እስካሁን እየተደረገ ላለው ድጋፍ የክልሉ መንግሥት ታላቅ አክብሮትና አድናቆት እንደሚሰጥ የገለጹት አቶ ግዛቸው ለሕዝቡ የሚደረገው ድጋፍና ርብርብ ሊቀጥል ይገባዋል ነው ያሉት፡፡
“አሸባሪው ቡድን በሕዝባችን ላይ ያደረሰው ጉዳት በገንዘብ የማይተመን አንዳንዱም በቁሳዊ ስሌት የማይተካ ሰብዓዊና ህሊናዊ ጉዳት ቢሆንም በጽኑ አንድነታችን ቁስን መተካት፤ ሥነ ልቦናን መልሶ መገንባት፤ ሕዝባችንንም መልሶ ማቋቋም እንችላለን፡፡ ስለሆነም ለዚሁ ተግባር እንደተለመደው ከሀገር ውጭም በሀገር ውስጥም ያለን ኢትዮጵያውያን ባለን አቅምና ሙያ ሁሉ ትኩረት ሰጥተን መረባረብ ይገባናል” ብለዋል፡፡
ዛሬም እንደሁልጊዜው በሁሉም የሀገሪቱ ጫፍ ያለ ኢትዮጵያዊ በወገን ላይ የደረሰውን ግፍና ሰቆቃ፤ ዝርፊያና ውድመት በተፈጸመባቸው አካባቢዎች በመገኘት ለወገን ደራሽ ወገን መሆኑንን በተግባር በማሳየት የኢትዮጵያን አሸናፊነት በተግባር ሊያረጋግጥ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
ወገኖችን ለመደገፍ ከአሁን በፊት የነበሩት የገቢ ማሰባሰቢያ የባንክ አካውንቶች እንዳሉ ሁኖ በኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን በኩል 9595 የSMS መልዕክት የተከፈተ በመሆኑ የሚፈልጉትን የብር መጠን በመላክ ድጋፍ እንዲያደርጉ የክልሉ መንግሥት ጥሪ ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡