በአማራ ክልል “የአንድ ሚሊዬን ዲያስፖራ ወደ ሀገር ቤት” መርሐ ግብር ይፋ ሆነ፡፡

0
74

ባሕርዳር፡ ታኅሣሥ 19/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) “አንድ ሚሊዬን ዲያስፖራ ወደ ሀገር ቤት” ጥሪን ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ ሀገር ቤት እየገቡ ነው፡፡ በተዘጋጀው መርሐ ግብር የዲያስፖራው አባላት የሽብር ቡድኑ በከፈተው ወረራ የተጎዱ አካባቢዎችን ተዘዋውረው ይመለከታሉ ነው የተባለው፡፡ መርሐ ግብሩ ታኀሣሥ 25/2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ እንደሚጀምር የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኅላፊ አቶ ጣሂር ሙሐመድ መርሐ ግብሩን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ መርሐ ግብሩ ታኀሣሥ 25/2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ ይጀመራል ብለዋል፡፡
የመጀመሪያዎቹ ቀናት መርሐ ግብር ከፌዴራል መንግሥት መርሐ ግብር ጋር ተጣጥሞ ተዘጋጅቷል ያሉት ቢሮ ኅላፊው ሌሎቹ መርሐ ግብሮች ግን በክልሉ በተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ የሚመሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ያለው መርሐ ግብር በሁለት ዙር የተከፈለ ሲሆን እስከ ጥር 6/2014 ዓ.ም ይቀጥላልም ተብሏል፡፡
መርሐ ግብሩ ታኀሣሥ 25/2014 ዓ.ም ጥዋት መነሻውን በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ አድርጎ ደብረ ብርሃን፣ ሸዋ ሮቢት እና አጣየ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን ይመለከታሉ፡፡ በዚያው ቀን ወደ ኮምቦልቻ በማቅናት በኮምቦልቻ የተጎዱ የመሰረተ ልማት ተቋማትን የይመለከታሉ ብለዋል አቶ ጣሂር፡፡
በተከታታይ ቀናት ከደሴ እስከ ቆቦ የሚደርስ ምልከታ የሚያደርጉት ዲያስፖራዎቹ ወደ ላል ይበላ ተመልሰው እስከ ሰቆጣ የሚደርስ ምልከታ በማድረግ የሽብር ቡድኑ ያደረሰውን ጉዳት ይመለከታሉ ነው ያሉት፡፡ አቶ ጣሂር ዲያስፖራዎቹ ከታኀሣሥ 28 እስከ 29/2014 ዓ.ም “ልደትን በላል ይበላ” እንደሚያከብሩ ገልጸው በመርሐ ግብሩ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ ተጋባዥ እንግዶች እና የእምነቱ ተከታዮች ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡
ታኀሣሥ 30/2014 ዓ.ም ከላል ይበላ ጋሽና፣ ነፋስ መውጫ እና ደብረ ታቦር የሚገኙ አካባቢዎችን ተመልክተው ወደ ባሕር ዳር ይገባሉ ብለዋል ቢሮ ኅላፊው፡፡ አቶ ጣሂር ከጥር 1 እስከ ጥር 5/2014 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ የኢግዚቪሽን እና ሲምፖዚየም መርሐ ግብር እንደሚኖር ገልጸው በመርሐ ግብሩ ክልላዊ እና ሀገራዊ አንድነት፣ መልሶ ግንባታ፣ በቱሪዝም እና በኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ምክክር ይደረጋል ብለዋል፡፡ የመርሐ ግብሩ የመጀመሪያ ዙር ፍፃሜ በባሕር ዳር ከተማ ጥር 5/2014 ዓ.ም በተዘጋጀው የአንድነት እና የትብብር እራት ግብዣ ፍፃሜውን ያገኛል ነው ያሉት፡፡
ሁለተኛው ዙር መርሐ ግብርም ከጥር 9/2014 ዓ.ም ጀምሮ በጎንደር እና አካባቢው እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!