በአማራ ክልል የሚተገበር የ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ፡፡

0
220

ባሕር ዳር፡ ጥር 02/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) በአማራ ክልል የሚተገበር የአምስት ዓመታት ፕሮጀክት ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ የድርጅቱ ዳይሬክተር ዶክተር አለማየሁ ዋሴ ዛሬ ከልዩ ልዩ ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች ጋር ስምምነቱን ተፈራርመዋል፡፡

አመልድ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ አደጋ በሚያጋጥም ጊዜ የዕለት ደራሽ ድጋፍ በማድረግ፣ በመልሶ ማቋቋም እና በልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች አማራ ክልልን የሚደግፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡

ይህ ድርጅት ከለጋሽ አካላት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት ለአምስት ዓመታት የሚተገበር የ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ስምምነት ዛሬ ተፈራርሟል፡፡ የፕሮጀክቱ መዳረሻ የኅብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ነው። ትኩረቱንም የመተዳደሪያ አቅምን በማሳደግ፣ የአመጋገብ ስርዓትን በማሻሻል እና የተቋማትን አቅም በማጎልበት ላይ አድርጎ ይሠራል ተብሏል፡፡

ተግባራዊ የሚደረገው ደግሞ በሰሜን ወሎ ዞን እና በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች ነው፡፡ በ207 ቀበሌዎች 217 ሺህ 879 ሰዎች ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም በፊርማ ሥነርስዓቱ ተገልጿል፡፡

ፕሮጀክቱ ቀደም ብሎ መጀመር ያለበት ቢሆንም በጸጥታ ችግር ምክንያት መዘግየቱ ተነስቷል፡፡ በተፈጠረው ወረራ ምክንያት ዕቅዱን ወደ መሬት ለማውረድ ሊያስቸግር እንደሚችል የተነሳ ሲሆን ፕሮጀክቱ የመልሶ ማቋቋም ሂደቱን ሊያግዝ በሚችል መልኩ እንደሚተገበር ተመላክቷል፡፡

የአመልድ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዓለማየሁ ዋሴ ‹‹ፕሮጀክቱ የሚተገበርባቸው ወረዳዎች አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጉዳት ያደረሰባቸው በመሆኑ በተለዬ የታሪክ አጋጣሚ ለድርጅቱ ትልቅ ፕሮጀክት ነው›› ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ስብራቱን ሊጠግን በሚችል መልኩ ተለዋዋጭ ባሕሪ እንዲኖረው ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩ ኤስ አይ ዲ) ፈቃድ መገኘቱንም አመላክተዋል፡፡ በመሆኑም በየአካባቢው ካሉ የመንግሥት አካላት ጋር በመደጋገፍ ውጤታማ ተግባራት እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡ ቀጣይም ሌሎች አካባቢዎችን ለማልማት እየተሠራ መሆኑን ነው ዶክተር አለማየሁ ያመላከቱት፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዶክተር አልማዝ ጊዜው እንዳሉት ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት በግብርና ላይ ልዩ ትኩረት አድርገው ከሚሠሩ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ የግብርናው ዘርፍ ውስብስብ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ በትብብር መሥራት እንደሚጠይቅም አመላክተዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግና ተቋማትን በማጠናከር ሕዝቡን በተጨባጭ ሊለውጥ እንደሚችልም አብራርተዋል፡፡ በመልሶ ግንባታው ሰፊ ሚና እንደሚኖረውም ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህም ቢሮው የቅርብ ትብብር፣ ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

ፕሮጀክቱ ለመንግሥት ተቋማት ተጨማሪ የገንዘብ ምንጭ ሆኖ የመፈጸም አቅማቸውን እንደሚያሳደግ የገለጹት ደግሞ የገንዘብ ቢሮ ምክትል ኀላፊዋ መሠረት አዱኛ ናቸው፡፡ ወይዘሮ መሠረት እንዳሉት እቅዱ የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖረው ፈራሚ ተቋማት በባለቤትነት መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም በየጊዜው እንደሚገመገምም ተናግረዋል፡፡ ገንዘብ ቢሮም ውጤታማነቱን በትኩረት ይከታተላል፣ ይቆጣጠራልም ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/