“በአማራ ክልል በአሸባሪው ቡድን የደረሰውን ጉዳት የተለያዩ ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓላትን ተጠቅሞ ለዳያስፖራውና ለሕዝቡ ለማስገንዘብና መልሶ ለመገንባት እየተሠራ ነው” የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ

0
106

ባሕር ዳር፡ ጥር 02/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የወደሙ መሰረተ ልማቶችና በክልሉ ሊለሙ የሚችሉ ፀጋዎችን የሚያሳይ አውደርእይ ለሁለተኛ ቀን በባሕር ዳር እየተጎበኘ ይገኛል። አውደርእዩ እየተጎበኘ የሚገኘው በዳያስፖራ፣ በክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችና በነዋሪዎች ነው። በክልሉ መንግሥት የተዘጋጀው አውደርእይ ላይ በአማራ ክልል በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የወደሙ መሰረተ ልማቶች፣ በክልሉ ሊለሙ የሚችሉ ፀጋዎች፣ የተለያዩ ባሕላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ቅርሳቅርስና ስእሎች እየተጎበኙ ነው።

የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ ጣሒር ሙሐመድ ሀገራዊ ጥሪን ተቀብለው ወደ አማራ ክልል የገቡ ዳያስፖራዎችን በመቀበል በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የወደሙ በርካታ መሰረተ ልማቶችን እንዲመለከቱ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

ክልሉ የተለያዩ ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓላትን ተጠቅሞ ለዳያስፖራው በማስቃኘት ዳያስፖራው የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ እየተሠራ ነው ብለዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ ሕዝቡና ዳያስፖራው በመገኘት በድምቀት መከበሩን ኀላፊው አስታውሰዋል።

ጥምቀትን በጎንደር፣ ጥር 23 የሚከበረው የአገው ፈረሰኞች በዓል፣ ጥር 13 በሰከላ የሚከበረው ግዮን በዓልና በወሎ ምድር በወጣቶች የሚከበረው ‘የአሁ ላሎ’ በዓልን በድምቀት ለማክበር ከፍተኛ ዝግጅት መደረጉን አቶ ጣሒር አስረድተዋል።

ጥር 7/2014 ዓ.ም የህልውና ዘመቻውን፣ የተጎዱ መሰረተ ልማቶች ተመልሰው በሚጠገኑበት ሁኔታ ላይ ምክክር ለማድረግ በባሕር ዳር ሲምፖዚየም እንደሚካሄድም አቶ ጣሒር ገልጸዋል። በሲምፖዚየሙ በክልሉ የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለዳያስፖራው ትውውቅ ይደረጋልም ብለዋል። በመኾኑም በሽብር ቡድኑ ምክንያት የወደሙ መሰረተ ልማቶችና የተጎዱ ዜጎች በተለይ በዳያስፖራው ወገኖቻችን መልሰው እንደሚቋቋሙ እምነታቸው መኾኑንም ኀላፊው ተናግረዋል። ከጥር 1 እስከ ጥር 7/2014 ዓ.ም በሚቆየው የፎቶ አውደርእይ መላው ሕዝብ በባሕር ዳር በተለምዶ አጠራር የቀድሞ ግዮን ሆቴል በመገኘት እንዲጎበኝ ጥሪ አድርገዋል።

ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/