በአማራ ክልል በተካሄደው 6ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ጥቃቅን ችግሮች ከመከሰታቸው ውጭ ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

0
57

በአማራ ክልል በተካሄደው 6ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ጥቃቅን ችግሮች ከመከሰታቸው ውጭ ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ
መጠናቀቁን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የክልሉ ፓሊስ ኮሚሽን የሰጠው መግለጫ ቀጥሎ ይቀርባል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ለ6ኛ ጊዜ ሀገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ እያካሄደች ትገኛለች። ይህ ምርጫ ሰላማዊ እንዲሆን ደግሞ የአማራ
ክልል ፖሊስ ከቅድመ ምርጫ ዝግጅት ጀምሮ እሰከ ዛሬ ድረስ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ፖሊሳዊ ተግባሩን እየተወጣ ይገኛል።
ዛሬ ምርጫ በተካሄደባቸው በክልላችን ከሚገኙ 15 ዞኖች መካከል በ9ኙ ዞኖች ከምርጫ ጋር በተያያዘ ወንጀል የፈፀሙ 26
ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራ የሚገኝ ሲሆን፤ በ6ቱ ዞኖች ግን ከምርጫው ጋር በተያያዘ ምንም አይነት
ወንጀል አልተከሰተም።
በዚህም በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ከተከሰቱ ችግሮች መካከል ጥቃቅን ችግሮችን ከምርጫ ቦርድ ጋር
በመወያየት ተፈተዋል። በምርመራ ላይ ከሆኑት ዋና ዋናዎቹ ከስር የተጠቀሱት ይገኙበታል፦
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በምዕራብ ደምቢያ ወረዳ በሚገኝ የምርጫ ጣቢያ በትናንትናው ዕለት አራት የምርጫ አስፈፃሚዎች
የምርጫ ቁሳቁስ የመጣበትን ሳጥን መከፈት በማይገባው ሰዓት በሕገወጥ መንገድ በመክፈታቸው በቁጥጥር ስር ውለው
ምርመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል። የምርጫ ቦርድም በትናንትናው ዕለት በዚሁ ወረዳ ዛሬ ላይ ምርጫ እንደማይካሄድበት
ማስታወቁ ይታወሳል።
በደቡብ ወሎ ዞን በተሁለደሬ ወረዳ በትናንትናው ዕለት የምርጫ ቁሳቁስ የመጣበትን ሳጥን ስድስት የምርጫ አስፈፃሚዎች
መከፈት በማይገባው ሰዓት በህገወጥ መንገድ በመክፈታቸው በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል።
የምርጫ ቦርድም በትናንትናው ዕለት በዚሁ ወረዳ የምርጫ ጣቢያ ቁጥር 1 እና ቁጥር 2 ዛሬ ላይ ምርጫ እንደማይካሄድባቸው
ማስታወቁ ይታወሳል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን ጃቢ ጠህናን ወረዳ ቀበሌ 16 ምርጫ ጣቢያ የቀበሌው ዋና አስተዳዳሪ በትናንትናው ዕለት የምርጫ
ቁሳቁስ የያዘውን ሰማያዊ ሳጥን ሰርቆ በመውሰድ ከውኀ ጉድጓድ ውስጥ የደበቀው ቢሆንም የፀጥታ ኀይሉ ባደረገው ማጣራትና
ክትትል ሳጥኑ ውኃ የማያስገባ በመሆኑ በውስጡ የነበረው ቁሳቁስ ሳይበላሽ ተገኝቶ በዛሬው ዕለት ምርጫው ተካሂዷል።
ተጠርጥረውም በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት ይገኛል። በዚህ የምርጫ ጣቢያ በፀጥታ አስከባሪነት የተመደበው
ፖሊስም ኀላፊነቱን ባለመወጣቱ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት ይገኛል።
በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ ልዩ ቦታው አጅሬ ጃኖራ ከተባለው አካባቢ በትናንትናው ዕለት ያልታወቁ ግለሰቦች ከምርጫ
ጣቢያው ድረስ በመሄድ በጥበቃ ላይ በሚገኙ የፀጥታ ኀይላችን ላይ ትጥቅ እንዲያወርዱ በማዘዝና ጥይት በመተኮስ የምርጫ
ቁሳቁስን ለመስረቅ እና ምርጫውን ለማስተጓጎል ያደረጉት ጥረት በፀጥታ ኀይላችን ተጋድሎና ቅንጅታዊ ስራ የፀረ-ሰላም
ኃይሎች ላይ ርምጃ በመውሰድ እኩይ ተግባር ከሽፎ በዛሬው ዕለት የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ ሆኖ ተጠናቋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ጨሌ ምርጫ ጣቢያ ላይ ዘበነ ለማ የተባለ የእናት ፓርቲ ተወካይ በድምፅ መስጫው
አካባቢ ወረቀት እየበተነ
ቅስቀሳ ሲያደርግ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ ተጣርቶበት በተፋጠነ የፍርድ ሂደት የምንጃር ወረዳ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው
ችሎት 8 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ወስኖበታል።
በሰሜን ሸዋ ዞን መንዝ ቀያ ወረዳ በምርጫ ጣቢያ 12 የብልጽግና ፓርቲ ተወካይ የሆነው አቶ ዳምጠው ያምጡ በዛሬው ዕለት
በምርጫ ጣቢያው አካባቢ ቅስቀሳ ሲያደርግ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተካሄደበት ይገኛል።
የክልላችን የፀጥታ ኀይል ፍፁም ገለልተኛ ሆኖ ፖሊሳዊ ተግባሩን በመወጣቱ በክልሉ ከሚገኙ 11 ሺህ 681 የምርጫ ጣቢያዎች
ውስጥ ከላይ ከተጠቀሱት ክስተቶች ውጭ በክልሉ የተካሄደው 6ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ ተጠናቋል።
ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ድርሻ ለነበራችሁ የክልላችን ሰላም ወዳድ ሕዝብ እንዲሁም ሌትና ቀን ያለ እረፍት
የሕዝብን አደራ ተቀብላችሁ የፀጥታ ተግባራችሁን ለተወጣችሁ አሁንም እየተወጣችሁ ላላችሁ የፀጥታ አካላት የአማራ ክልል
ፖሊስ ኮሚሽን ምስጋና አቅርቧል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here