“በአማራ ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ የሚቆምበት መቸ ነው?” የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት

0
571

“በአማራ ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ የሚቆምበት መቸ ነው?” የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 14/2013 ዓ.ም (አብመድ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ
ስብሰባውን እያካሄደ ነው፡፡ የምክር ቤት አባላትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ማብራሪያ እንዲሰጡባቸው
ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የነበረው የሕግ የማስከበር ዘመቻ ውጤታማ መሆኑን የምክር ቤት አባላት ተናግረዋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዜጎች የደረሰባቸውን ችግር መንግሥት በወሰደው ርምጃ መሻሻል መኖሩንም አንስተዋል፡፡ ይሁን እንጂ
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የኢትዮጵያን ሠላም በማይፈልጉ በዋናነትም በኦነግ ሸኔ እና በትህነግ የተቀናጀ ሴራ በሰሜን ሸዋ
የተለያዩ አካባቢዎች በዋናነትም በአጣየ፣ በማጀቴ፣ በሸዋሮቢትና አካባቢው በዜጎች ላይ የሕይወት መጥፋት፣ መፈናቀል፣ ንብረት
መውደም መከሰቱን አንስተዋል፡፡ ይሕ የሆነው የአማራ ክልል መንግሥት ሕግ የማስከበሩን ሥራ ከመንግሥት ጎን ሆኖ እየተወጣ
ባለበት ወቅት እንደሆነ ያነሱት የምክር ቤት አባላት፤ በዚህም ዜጎች ለችግር ተጋልጠዋል ብለዋል፡፡
ችግሩ ብሔር ተኮር ነው፤በተለይም በአማራ ላይ ተከታታይ የሕይወት መጥፋት፣ መፈናቀል፣ በሀገሩ እንዳይኖር የማድረግ
ተከታታይ ጉዳት እየደረሰበት ነው ብለዋል፡፡
መንግሥት ባለው የመረጃ ሰንሰለት እንደዚህ አይነት ችግር እንደሚደርስ አውቆ ዜጎች ችግር ሳይደርስባቸው ቀድሞ ለምን
መከላከል አልተቻለም በሚል በሕዝብ ዘንድ ጥያቄ እየተነሳ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በአማራ ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ የሚቆመው መቸ ነው ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ ችግሩ በተለይ በተያዘው ዓመት ዜጎች በተከታታይ
አሰቃቂ ግድያ፣ ማፈናቀል፣ የንብረት ውድመት እየደረሰባቸው ነው ብለዋል የምክር ቤት አባላት፡፡ ችግሩ ከሚፈጠርባቸው የክልል
መንግሥታት ጋር በመሆን ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመፍታት የመንግሥት ቁርጠኛ አቋም ምን እንደሆነ ማብራሪያ እንዲሰጥበት
ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here