“በንግግር ብቻ የሚፈታ ችግር የለም፣ ችግር የሚፈታው በተግባር ነው” በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ ስዩም መኮንን

155
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ

ባሕር ዳር: መጋቢት 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በትራኮማ በሽታ ምክንያት የዓይን ቆብ ፀጉር መቀልበስ ችግር ተጠቂ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ያለመ መድረክ በባሕርዳር ተካሂዷል። የትራኮማ በሽታን ከክልሉ መቆጣጠር እና ማጥፋት እንደሚገባ በመድረኩ ተመላክቷል።
በመድረኩ የተገኙ የዞን አስተዳዳሪዎች፣ ከንቲባዎች እና የጤና መምሪያ ኀላፊዎች የክልሉ ጤና ቢሮ ባስቀመጠው መሠረት ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሠሩ ገልፀዋል። የክልሉ ጤና ቢሮ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ የሥራ ኃላፊዎች የትራኮማ በሽታን መከላከል እና መቆጣጠር ላይ ለመሥራት ላሳዩት ቁርጠኝነት እና ለገቡት ቃል አመስግነዋል። የክልሉ ጤና ቢሮም በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል። ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ በሚቻለው ልክ ድጋፍ እንደሚደረግ ነው የተናገሩት። ቃላቸውን እንዲተገብሩና በቁርጠኝነታቸው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ ስዩም መኮንን የትራኮማ በሽታ በዚህ ከቀጠለ በርካታ ዜጎችን ለዓይነ ሥውርነት ይዳርጋል ነው ያሉት። የትራኮማ በሽታን መከላከል ካልተቻለ ከፈተኛ የሆነ ማኅበራዊ ጫና እንደሚፈጥርም ገልፀዋል።

ለአማራ ክልል የሚመጥን ሥራ በመስራት ትራኮማን ከክልሉ ማስወገድ ይገባልም ነው ያሉት። የሕዝብ ልጅ ነኝ ያለ ሁሉ የአማራ ክልል ሕዝብን ከትራኮማ ነፃ የማድረግ ሥራ መሥራት ይገባዋልም ብለዋል።

ልናድነው በምንችለው በሽታ የአንድ ሰውም ዓይን ሊጠፋ አይችልም በሚል ቁርጠኝነት መሥራት ይገባል ነው ያሉት። በቁጭት እና በእልህ መሥራት ከተቻለ ችግሩን መፍታት ይቻላልም ብለዋል።
ሀብትን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም ተናግረዋል። ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር በቅርበት በመሥራት ችግሮችን መፍታት ይገባል ብለዋል። ሥራዎችን በቁርጠኝነት እና በዘላቂነት መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። በንግግር ብቻ የሚፈታ ችግር የለም፣ ችግር የሚፈታው በተግባር ነው፣ የማኅበረሰቡን ችግር መፍታት የሚቻለው በመድከምና በተግባር ሠርቶ በማሳየት ነውም ብለዋል። በዘርፉ ጥብቅ የሥራ ክትትል በማድረግ በትጋት ለሚሠሩ አካላት እውቅና እንደሚሠጥም አስታውቀዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!