በኅብረተሰቡ የቀረቡ 24 የሙስና ወንጅል ጥቆማዎች ‹‹በትክክል ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል›› ተብሎ ምርመራ እየተደረገባቸው መኾኑን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ፡፡

255
ባሕር ዳር: ሕዳር 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሙስናን ጉዳይ በአዋጅ ኀላፊነት ከተሰጠው ጊዜ ጀምሮ የምርመራ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡
በኮሚሽኑ የሙስና ወንጀል ምርመራ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር አግራሩ አሊ እንዳሉት አንድ ግለሰብ ከሙስና ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በአካል፣ በስልክና በኢሜል ጥቆማዎችን ማቅረብ ይችላል፡፡
የሙስና ምርመራ ከዚህ በፊት በጸረ ሙስና ቢሮ በኩል ሲጣራ እንደነበር ያነሱት መምሪያ ኀላፊው ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በአዋጅ ቁጥር 263/2012 መሠረት የምርምራ ሂደቱን በፖሊስ፣ የመክሰስ ስልጣንን ደግሞ በአቃቢ ሕግ በኩል እንዲካሄድ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ኀላፊው እንዳሉት የሚሰጡ ጥቆማዎች በፖሊስ በኩል ወደ አንድ ቋት እንዲገቡ ተደርጎ በትክክል የሙስና ወንጀል መኾናቸው ይጣራል፤ ጥቆማው የሙስና ወንጀል መኾኑ ከተረጋገጠ ወደ ምርመራ ይገባል፡፡ በዚህም መሠረት የሙስና ጉዳይ ለፖሊስ በአዋጅ ከተሠጠው ጀምሮ ጥቆማዎችን ተቀብሎ የምርመራ ሥራ እያከናወነ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
በ2015 በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የቀረቡት 24 ጥቆማዎች ‹‹በትክክል ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል›› ተብሎ ምርመራ እየተደረገባቸው መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ ሰባቱ ጉዳዮች ተጣርተው ወደ አቃቢ ሕግ መላካቸውን አስረድተዋል፡፡
ጥቆማ የሰጡ የኅብረተሰብ ክፍሎችም በአዋጅ ቁጥር 699/2003 በፍትህ ቢሮ በኩል ከለላ እንደሚደረግላቸው ኮማንደር አግራሩ ነግረውናል፡፡
ከለላ የሚደረገው ጥቆማ አቅራቢው የሰጠው ጥቆማ ተጣርቶ አቃቢ ሕግ ክስ ሲመሰርትና በክርክር ላይ ሲኾን፣ ጥቆማ አቅራቢውም በፍርድ ቤትና በፖሊስ ላይ ቀርቦ የመሰከረ መኾኑ ሲረጋገጥ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ የተሰጠውን ከለላም ፖሊስ ያስፈጽማል፡፡
ከለላውም ጥቆማ አቅራቢው በሚያቀርበው የድጋፍ ጥሪ ፈጥኖ በመድረስ ወይንም ከአካባቢው የጸጥታ አካል ጋር የቅርብ ግንኙነት በመፍጠር በሚደረግ ጥበቃ አማካኝነት ሊኾን ይችላል ብለዋል፡፡
በዚህ መሰረት ማኅበረሰቡ ሙስና በሀገር ላይ አደጋው ከባድ መኾኑን ተገንዝቦ ያየውንና የሰማውን ለፖሊስ ኮሚሽን ወይንም ለኮሚሽኑ የሙስና ወንጀል የምርመራ ዘርፍ በአካል፣ በስልክ እና በኢሜል ጥቆማዎችን በመስጠት የተጀመረውን የጸረ ሙስና እንቅስቃሴ ውጤታማነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!