በኅብረተሰቡ እና በአልማ ለሚገነባው 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ፡፡

0
288

የትምሕርት ቤቶችን ጥራት ለማስጠበቅ እየሠራ መሆኑን የምስራቅ ጎጃም ዞን ትምሕርት መምሪያ አስታውቋል፡፡

በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ ደረጃውን የጠበቀ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለማስገንባት ዛሬ የመሠረተ ድንጋይ ተቀምጧል፡፡ በወረዳው እነገሽ በተባለ ቀበሌ ውስጥ ለሚገነባው ትምሕርት ቤት የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) እና ኅብረተሰቡ ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ በመርሀ ግብሩ ላይ እንደተገለጸውም ከጠቅላላ ወጪው ከ 5 መቶ ሺህ ብር በላይ የሚሆነው በኅብረተሰቡ የሚሸፈን ይሆናል፡፡

የምስራቅ ጎጃም ዞን ትምሕርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ዜና ገብረማሪያም በዞኑ በአልማ እና በኅብረተሰቡ ድጋፍ 12 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለማስገንባት እንደታቀደ ገልጸዋል፡፡

የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ አቶ ኑርልኝ ብርሃኑ ደግሞ የኅብረተሰቡን ተነሳሽነት በመጨመር ትምህርት ቤቱን በአጭር ጊዜ አስገንብቶ ለማጠናቀቅ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው ያለው የመንገድ ችግር እንዲቀረፍ ኅብረተሰቡ ጠይቋል፡፡   ምክትል አሥተዳዳሪውም ችግሩን ለመፍታት ዞኑ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል የትምህርት ቤቶች የጥራት ደረጃ 16 በመቶ ላይ እንደሚገኝና ይህንን ወደ 50 በመቶ ለማሳደግ የሦስት ዓመታት የለውጥ ዕቅድ አስቀምጦ ወደ ሥራ መግባቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ዘጋቢ፡- የኔነህ ዓለሙ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here