በኃይል ተሸካሚ ምሰሶ ላይ በደረሰ ስርቆት ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንደደረሰበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

0
254

በኃይል ተሸካሚ ምሰሶ ላይ በደረሰ ስርቆት ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንደደረሰበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል
አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 24/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከጢስ ዓባይ ኃይል ማመንጫ ወደ ባሕር ዳር 91 የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች
ተዘርግተዋል። ከእነዚህ የኃይል መስመር ተሸካሚዎች ስምንቱ የስርቆት ወንጀል እንደተፈጸመባቸው ድርጅቱ አስታውቋል።
አርሶአደር ተላይነህ ወንዴ በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የሰባታሚት ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ከወደቁ ምሰሶዎች አንዱ በማሳቸው
ዳር ይገኛል። በምሰሶዎቹ ላይ ስርቆት የተፈጸመው መጋቢት 21/2013 ዓ.ም እንደሆነም ነው የነገሩን፡፡ በወቅቱ በምሰሶዎቹ ላይ
ስርቆት መፈጸሙንም ማሳወቃቸውን አርሶአደሩ ጠቁመዋል።
በሰባታሚት ቀበሌ የቀበሌ ኦፊሰር ረዳት ሳጅን ልቅናው ደሣለኝ የስርቆት ወንጀሉን ማኀበረሰቡ እንዲያጋልጥ እና ድርጊቱ
እንዳይደገም ከማኅበረሰቡና ከጸጥታ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልም ያገለገሉና ሊነሱ የሚገባቸው የኃይል መስመሮችን ጥቆማው እንደደረሰው ሊያነሳ እንደሚገባው
ረዳት ሳጅን ልቅናው አሳስበዋል። ማኅበረሰቡም በአካባቢው የሚገኘውን የኃይል ማስተላለፊያ ምሰሶ በባለቤትነት መጠበቅ
እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የጥገና ክፍል ቡድን መሪ ታደሠ ሞገስ ድርጅታቸው በዓመት ሁለት ጊዜ የመስመር ደኅንነትን ፍተሻ
እንደሚያካሂድ አስረድተዋል። ከጢስ ዓባይ ባሕር ዳር የተዘረጋውን መስመር ኅዳር/2013 ዓ.ም ምልከታ እንዳደረጉና ምንም
አይነት የመስመር ችግር እንዳላዩበት ጠቁመዋል።
ከተዘረጉት አጠቃላይ ምሰሶዎች ስምንቱ ላይ ስርቆት ስለተፈጸመባቸው አሁን ላይ ኃይል ተቋርጧል ያሉት አቶ ታደሠ በተቻለ
መጠን አገልግሎቱ ለማስጀመር እየሠሩ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ለጉዳት የተጋለጡት ምሰሶዎች 33 ሜጋዋት የተሸከሙ እንደነበሩ ጠቁመዋል። በደረሰው ጉዳት ለጠጋኞችና ለጥበቃ ከሚወጣው
ወጪ በተጨማሪ ድርጅቱ 16 ሚሊዮን ብር ለኪሳራ እንደተጋለጠ ቡድን መሪው ገልጸዋል።
የተዘረጉት መስመሮች በስርቆትም ሆነ በተለያየ አጋጣሚ ብልሽት ቢያጋጥማቸው ተጎጂው ማኅብረተሰቡ በመሆኑ ጥበቃ
ሊያደርግላቸው እንደሚገባ አቶ ታደሠ አስገንዝበዋል። በየወቅቱ ጥገና ቢደረግም ተመልሶ እየተሰረቀባቸው እንደሆነ የተናገሩት
ቡድን መሪው ደብረ ማርቆስን ጨምሮ በርካታ አካባቢዎች የመስመር ስርቆት እየተከሰተ ስለሆነ መንግሥት አስፈላጊውን ጥበቃ
ሊያደርግ እንደሚገባ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:- ብሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m