በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጸመ ጥቃት የሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አረጋገጠ፡፡

0
408

ባሕር ዳር፡- ጥር 13/2012ዓ.ም (አብመድ) በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወምበራ ወረዳ ኮንግ ቀበሌ ማዕከል በተፈጸመ ጥቃት የሰዎች ሕይወት ማለፉን ፌዴራል ፖሊስ አረጋግጧል፡፡

ድርጊቱ የተፈጸመው ጥር 8/2012 ከቀኑ 10፡00 አካባቢ እንደሆነ ነው ነዋሪዎቹ እና የሥራ ኃላፊዎቹ የተናገሩት፡፡ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ጉዳዩን እንደሰማ ለማጣራት እና መረጃ ለማግኘት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ከጥር 11/2012 ጀምሮ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ አካባቢው ገብተው እያረጋጉ እንደሆነ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የመተከልና አዊ ብሔረሰብ አካባቢዎች አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ኢብራሂም ሙሃመድ ለአብመድ ገልጸዋል፡፡

እስካሁን ባላቸው መረጃ መሠረት በአካባቢው ነዋሪዎች በተፈጸመው ጥቃት የሦስት ሰዎች ህይዎት ማለፉንም ዋና ኢንስፔክተር ኢብራሂም ተናግረዋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ግን የሟቾች ቁጥር ፖሊስ ከሰጠው መረጃ እንደሚበልጥ ነው የተናገሩት፡፡ ጥቃቱ የተፈጸመበትን ምክንያት ለማወቅና ተርጣሪዎችን ለመያዝም ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ነው ያስታወቁት፡፡

የብልጽግና ፓርቲ አባልና በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአማራ ክልል አስተባባሪ አቶ ተመስገን ኃይሉ ድርጊቱ ስለመፈጸሙ መረጃው አላቸው፡፡ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ግን ግልጽ መረጃ እንደሌላቸው ተናገረዋል፡፡ ጉዳዩን ለማጣራት እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ተመስገን በሽምግልና ለማረጋጋት ጥረት እየተደረገ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በፊት ግጭት ተከስቶባቸው በነበሩ ሦስት የቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወረዳዎች የአማራ እና ቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሥራ ኃላፊዎች የእርቀ ሰላም ውይይቶችን እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡ እስካሁንም ማንዱራ እና ዳንጉር ወረዳዎች ላይ እርቀ ሰላም ተካሂዷል፡፡ ጉባ ወረዳ ላይም እርቀ ሰላም ተጀምሯል፡፡ በዚሁ ወረዳ አልመሃል እና አጉልታ በተባሉ ማዕከላትም በቅርቡ እርቀ ሰላም እንደሚካሄድ ነው አቶ ተመስገን የገለጹት፡፡

ከዚህ ቀደም የተከሰቱ ግጭቶች ያስከተሉትን ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት በማውገዝ እና ከሂደቱም በመማር ለሰላም እየተሠራ ባለበት ወቅት የሰሞኑ ድርጊት መከሰቱ ያልታሰበ እና አሳዛኝ መሆኑን የተናገሩት አቶ ተመስገን ክስተቱ በሌሎች አካባቢዎች ሥጋት እንዳይፈጥር እየተሰራ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ወምበራ ወረዳ ከዚህ በፊት ብሔርን መሠረት ያደረገ ግጭት እንዳልተፈጠረበትም የመረጃ ምንጮቻችን እና የሥራ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ሰላም የነበረ ቀጣና ላይ ከሰሞኑ የተከሰተው ድርጊት እንዴትና ለምን እንደተፈጸመ ግን አሁንም መጣራትና መታወቅ፣ አጥፊዎችም እንዲጠየቁ ማድረግ ይፈገባል ነው ያሉት፡፡ አብመድ ድርጊቱን በተመለከተ ከክልሉ የሥራ ኃላፊዎች መረጃ ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም አልተሳካም፡፡

ዘጋቢ፡- አስማማው በቀለ