በቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በዜጎች ላይ እደረሰ ያለውን ግድያ ለመከላከል ወሳኝና አስቸኳይ አቅጣጫ መቀመጡን የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ፡፡

348
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ
በቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በዜጎች ላይ እደረሰ ያለውን ግድያ ለመከላከል ወሳኝና አስቸኳይ አቅጣጫ መቀመጡን የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 11/2013 ዓ.ም (አብመድ)
ፓርቲው በፌስ ቡክ ገጹ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ሙሉ መግለጫው ቀጥሎ ይቀርባል።
በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ያወጣው መግለጫ!
በሬ ሆይ በሬ ሆይ …… !
ግንዱን ከቆረጥነው አንጓውን እናከስመዋለን !
የምንገኝበት የፖለቲካ መድረክ ሀገር አፍራሽ ከሀዲዎች እየፈረሱ የሚገኙበት ታሪካዊ መድረክ ነው። የግፈኞች ፀሀይ እየጠለቀች የግፉአን ጀንበር እየወጣች በምትገኝበት በዚህ ታሪካዊ መድረክ ላይ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ ወገን ከሀዲውና ወንበዴው ትህነግና የጥፋት አጋሮቹ በሌላ ወገን የሚፋለሙበት አውደውጊያ ላይ እንገኛለን።
በዚህ ወሳኝና ታሪካዊ መድረክ ላይ ጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን ከአማራና ከአፋር ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ጋር በመተባበር አንጸባራቂ ድል እያስመዘገበ ይገኛል።
ይሁን እንጂ የአውደውጊያውን አቅጣጫ ለማስቀየር በቤንሻንጉል ክልል በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለውን ወከባና የጠላት ኃይል እየፈፀመብን ያለውን አረመኔያዊ ጥድፍያ ሳንሸራርፍ እንረዳለን። የኦሮምያ ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ያሳረፈበትን ጠንካራ ክንድ መቋቋም አልችል ብሎ በሽሽት ቤንሻንጉል ክልል የከተመው ኦነግ ሽኔና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ህዝብ ነጻ አውጭ ነኝ የሚለው አማፂ ቡድን ከከሀዲው ትህነግ የሚሰፈርለትን መቅኖን ተጠቅሞ እስከዚች ሰአት ድረስ ያወጀብንን ጦርነት በውል እንገነዘባለን።
በዚህ ሰአት በግፍ የሚገደሉ ፣ የሚዘረፉ የሚሰደዱ ወገኖቻችን ጉዳይ ያሳስበናል። በህዝባችን ላይ የሚፈጸመውን ግፍ የሚቃወሙ የክልሉ ተወላጆች (በተለምዶ ቀይ የሚባለውና ቅን አሳቢና ለወገን ተቆርቋሪ የሆኑ የጉሙዝ ሽማግሌዎች) ላይ የሚፈጸመው አረመኔያዊ ግድያም የወንበዴው ህወሓት ምህረት የለሽ አስተምህሮ ምን ያህል እንደበዘበዛቸው እየታዘብን ነው። ድርጊቱና የድርጊቱ አፈጻጸም የዘገነናቸውና የወገኖቻቸው እልቂት ያሳሰባቸው የፖለቲካ ኃይሎችና የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች የሚያቀርቡትን ቅሬታና ሂስ በአክብሮት የምንቀበለው ነው።
ይሁን እንጂ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ድባጤ ወረዳ:- ሳምቦሰሪ ቀበሌ፣ አልባሳን ቀበሌ ፣ ጋፋሪ ቀበሌ ፣ ሙዘን ቀበሌ ፣ቆርቃ ቀበሌ፣ ድባጤ ከተማ፣ ዛሬ ደግሞ ማንዱራ ቁጥር 1 እና ጅግዳን እንዲሁም ሌሎች በስም ያልተጠቀሱ አካባቢዎች ላይ የተፈጠረው የጅምላ ጭፍጨፋና የዘር ማጥራት ወንጀል ከወንበዴው ህወሓት ጋር የተጀመረውን አመክንዮአዊ ግንባር ለማስቀየስ ፣ ኃይል ለመበተን ፣ የግንባሩን ስረ-ምክንያት ሌላ መልክ እንዲይዝ ለማድረግ ፣ በወንበዴው ቡድን የተጀመረው የእብሪተኞች የጦርነት ትንኮሳና ሀገራዊ ክህደት በአለም አደባባይ እየተጋለጠ ባለበት በዚህ ወቅት ለህግ የበላይነት መከበርና ለሀገር አንድነት መጠበቅ የተጀመረውን ራስን የመከላከል ፍትሀዊ ጦርነት ወደእርስ በእርስ ጦርነት አዙሪት ውስጥ ለማስገባት ጠላት ያልሞከረው ሙከራ የለም።
ነገም በየትኛው አቅጣጫ ምን አይነት ትንኮሳ ሊያጋጥም እንደሚችል በተጨባጭ መገመት አይቻልም። የጠላት የጣረሞት ትንቅንቅ ላልተወሰነ ጊዜም ቢሆን መፍጨርጨሩ አይቀርም። ትላንትም በእብሪት አጥፊ ክንዳቸውን አንስተው ያለሙት ሳይሳካ ሲቀር ጩኸታችንን እየተቃሙ ሲንደፋደፉ እየተመለከትናቸው ነው።
የሰሜን ዕዝን በክህደት በትራቸው ያለእርህራሄ ከቀጠቀጡ በኋላ የማንነትና የወሰን ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች የክልላችንን ህዝብ በማዋረድ ጎንደርንና ወልድያን በአንድ ለሊት ለመቆጣጠር አቅዶ ጦርነት ያወጀውን የትህነግ ከሀዲ ስብስብ ተአምራዊ በሆነ የጦር ጀብዱ ያንበረከከውን ጥምር ኃይል (ጀግናውና ባለግርማ ሞገሱ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ፣ ተአምረኛው የአማራ ልዩ ኃይልና የቁርጥ ቀን ደራሹ የአማራ ሚሊሻ) ተስፋፊና እርስት አስመላሽ በሚል የተሸናፊነት ስነ-ልቦና እየከሰሰው ይገኛል።
ለክሱ ህጋዊ፣ ሞራላዊና ፖለቲካዊ ተቀባይነት ያግዘኛል ያለውን የቤንሻንጉል መተከል የጅምላ ጭፍጨፋና የዘር ማጥራት ወንጀል ጠዝጣዥና፣ ዘግናኝና ስሜት ቀስቃሽ የጦርነት ገፊ ምክንያት በማድረግ እየተጠቀመበት ይገኛል። ትህነግ ፣ ኦነግና የቤንሻንጉል ጉሙዝ አማፂ ቡድን የቀደደልንን ቦይ ተከትለን የምንፈስ ከሆነ “በሬ ሆይ በሬ ሆይ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” እንዲሉ ከገባበት የሞት ጣር ትንቅንቅ በመውጣት ድል የሚቀዳጀው ወንበዴው ቡድን ብቻ ነው። ስለሆነም የተዘጋጀልንን ወጥመድ በውል ተገንዝበን ያጋጠመንን ታሪካዊ አጣብቂኝ በስሜት ሳይሆን በስሌት ማለፍ ይኖርብናል።
ይኸ ማለት አንድ አንድ የፖለቲካ ኃይሎችና የማህበራዊ ድረ-ገጽ ትስስር አንቂዎች እንደሚሉት የሰሜኑ ግንባር እስኪጠናቀቅ ድረስ ህዝቡ ይለቅ ማለት አይደለም። በቦታው ያለው የመከላከያ ሰራዊትና የክልሉ ልዩ ኃይል እንደአስፈላጊነቱም በየጊዜው የሚቀመጡ አቅጣጫዎችን ታሳቢ ያደረገ የመከላከል ስራ እንዲሰራ ወሳኝና አስቸኳይ አቅጣጫ ተቀምጧል።
ስለሆነም የክልሉ መንግስትም ሆነ የፌዴራል መንግስት እየተከተለ ያለው አማራጭ ትክክለኛውን መንገድና ዘላቂውን አማራጭ ስለሆነ ይህንን ውሳኔና የመንግስት ልዩ ትኩረት ተረድተን ዋነኛው የሀገርና የህዝብ ጠላት ግብአተ መሬቱ ሲረጋገጥ ግንዱን ተጣብቀው ያቀጠቀጡ አንጓዎች ከግንዱ ጋር አብረው የሚከስሙ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።
ሳሩን እያየን ገደል አንገባም !
ድል ለግፉአን !
ኢትዮጵያንን እና ህዝቦቿን ፈጣሪ ይባርክ !
11/03/2013 ዓ.ም.
ባህር ዳር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here