በባሕር ዳር ከተማ የሚገነቡ መሠረተ ልማቶች በሚፈለገው ጥራት ልክ ሊከናወኑ እንደሚገባ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

0
62
በባሕር ዳር ከተማ የሚገነቡ መሠረተ ልማቶች በሚፈለገው ጥራት ልክ ሊከናወኑ እንደሚገባ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2013 ዓ.ም (አብመድ) የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በከተማዋ እየተከናወነ የሚገኘዉን የመሠረተ ልማት ግንባታ ምልከታ አድርጓል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በየክፍለ ከተማው በመዘዋወር የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የውኃ ማፋሰሻና ድልድዮች ግንባታ ያሉበትን ሁኔታ ቃኝቷል። በቅኝቱም የግንባታ ጥራት ላይ ትኩረት አድርጓል።
የአብመድ የጋዜጠኞች ቡድንም ከቋሚ ኮሚቴዎች ጋር በመዘዋወር የመሠረተ ልማት ግንባታዎቹ ያሉበትን ሁኔታ ምልከታ አድርጓል።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በ2013 በጀት ዓመት 13 ነጥብ 25 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት አቅዶ እየሠራ እንደሆነ ከተማ አስተዳደሩ ገልጿል። በከተማዋ ቀደም ሲል የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ግንባታ ያልተሠራላቸው አካባቢዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው ሥራም እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
ወይዘሮ የሺወርቅ በላይ በባሕር ዳር ከተማ የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ክፍለ ከተማ የኤፍራታ አካባቢ ነዋሪ ናቸው። ክረምት ሲገባ የሚፈጠረው ጭቃ ለመውጣትና ለመግባት አዳጋች ሲሆንባቸው እንደቆየ አስታውሰዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የጌጠኛ ድንጋይ መንገድ ሊገነባላቸው እንደሆነ ሲሰሙ መደሰታቸውን ገልጸው ሥራውን በገንዘብ፣ በሀሳብና በጉልበት እየደገፉ እንደሆነም ወይዘሮ የሺወርቅ ነግረውናል።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር መንገድ ባለሥልጣን ጽሕፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አብቧል ሙላት በዘንድሮው በጀት ዓመት በዓለም ባንክ፣ በክልሉ መንግሥትና በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በጀት 13 ነጥብ 25 ኪሎ ሜትር የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ ከተፋሰስ ጋር እየሠሩ እንደሆነ አስረድተዋል። ሁለት ድልድዮችና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችም ጎን ለጎን እየተሠሩ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የሚከናወኑ ሥራዎችን ጥራት በተመለከተ ከየአካባቢው ነዋሪዎች የተውጣጣ ግብረ-ኀይል ክትትል እያደረገ መሆኑን ምክትል ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል። በግብረኃይሉ ጥቆማ መሠረት ስህተት ከመፈጠሩ በፊት የማስተካከያ ሥራዎችን መሥራታቸዉን አቶ አብቧል ተናግረዋል።
የመንገድ ሥራዎች በሚከናወኑበት ወቅት የውኃ መስመር መፈንዳት፣ የመብራት ፖል መጎዳትና የስልክ መስመር መቆራረጥ እንደነበረ የጋዜጠኞች ቡድኑ በምልከታው አረጋግጧል፤ ይሁን እንጂ ሥራውን ከመጀመራቸው አስቀድሞ ለየተቋማቱ ደብዳቤ እንደፃፉና ጽሕፈት ቤታቸው የካሳ ክፍያን ቢፈጽምም ተቀናጅቶ የመሥራት ችግር እንደሚስተዋል ምክትል ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል።
13 ነጥብ 25 ኪሎ ሜትር የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ 7 ኪሎሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታና ሌሎች ሥራዎችን ለማከናወን 526 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ስማቸው ንጋቱና ሌሎች የምክር ቤት አባላት የሚገነቡትን መሠረተ ልማቶች ጥራት ዛሬ በከተማዋ በመዘዋወር ተመልክተዋል። ቋሚ ኮሚቴው የሚሠራው መንገድ በዲዛይኑ መሠረት መከናወኑንና አለመከናወኑ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ በየጊዜው ክትትል ያደርጋል ብለዋል።
“ባሕር ዳር በመሠረተ ልማቶች በኩል ብዙ ይቀራታል፤ በተለይ የማስፋፊያ ከተማ ተብለው የሚጠሩት አፄ ቴዎድሮስና ዳግማዊ ምኒልክ ክፍለ ከተማዎች በርካታ የመሠረተ ልማት ክፍተት አለባቸው። ቤቶች ተገንብተው መውጫ መንገድ የሌላቸው፣ በክረምት በጭቃ የሚሰቃዩ በርካታ አካባቢዎች አሉ” ብለዋል።
የሚገነቡትን መሠረተ ልማቶች ለመቃኘት በበጀት ዓመቱ ሁለት ጊዜ መሰማራታቸዉን ያስታወሱት አቶ ስማቸው ዛሬ ባካሄዱት ቅኝት ባመዛኙ የተሻለ ጥራት ያለው ሥራን ማየታቸው አስረድተዋል። ቀደም ሲል ባደረጉት የመስክ ምልከታ ከጥራት አኳያ ግንባታውን እያከናወነ ላለው አካል እንዲስተካከል የተሰጠው አስተያየት በዛሬው ቅኝት ተስተካክሎ ማየታቸውን ነው የነገሩን። ይሁን እንጂ የመሠረተ ልማቶቹ ግንባታዎች በሚፈለገው ጥራት ሊከናወኑ እንደሚገባ አቶ ስማቸው አሳስበዋል።
በክፍለ ከተሞች ተቀናጅቶ የመሥራት ክፍተት እንዳለ የጠቆሙት የምክር ቤቱ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው ተቋማት በቅንጅት እንዲሠሩ፣ የመንገድ ሥራዎችም ክረምት ከመቃረቡ በፊት አስቀድሞ መጀመር እንዳለበት ምክረ ሀሳብ መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡ የመንገድ ግንባታዎቹ በየካቲት መጨረሻ አካባቢ መጀመራቸው ትክክል እንዳልሆነና መደገም እንደሌለበትም ነው ያሳሰቡት።
ዘጋቢ:- ብሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here