በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በ34 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀክት ለአገልግሎት በቃ፡፡

0
50

በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በ34 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀክት ለአገልግሎት በቃ፡፡

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ለዓመታት በሰባታሚት ቀበሌ አካባቢ ከከተማዋ የሚወጣው ደረቅ ቆሻሻ በመከማቸቱ በአካባቢው ላይ ብክለት ሲያስከትል ቆይቷል። ይህንን እና መሰል ችግሮችን ይቀርፋል የተባለለት እና በጃፓን፣ በስዊድን እና በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በተመደበ በ34 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ የሙከራ ፕሮጀክት ዛሬ ተመርቋል፡፡

ዶክተር ብርሃኑ እስከዚያ የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ናቸው፤ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ሥራ ለማከናወን 23 ሺህ ኪዩቢክ ሜትር ቆሻሻ መጠቀማቸውን አስረድተዋል። የደረቅ ቆሻሻ ማጣሪያው 10 ነጥብ 5 ሜትር ስፋት አለው፤ 650 ሜትር ቱቦዎች በውስጡ መዘርጋቱን ዶክተር ብርሃኑ ገልጸዋል።

ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ የሙከራ ፕሮጀክቱ ለስድስት ዓመታት አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል።

የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ቴክኖሎጂው ቆሻሻ በባክቴሪያ አማካኝነት በመብላላት በፍሳሽ መልኩ የሚወገድ በመሆኑ የካርበን ልቀትን ለመቀነስ የጎላ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡

የኢፌዴሪ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ እንደዚህ አይነት ፕሮጀክት የከተሞችን የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ያዘምናል ነው ያሉት። ፕሮጀክቱ ከሚሰጠው ጠቀሜታ አንጻር ብዙ ወጪ ያልወጣበትና ብዙ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠይቅ መሆኑ የበለጠ አዋጭ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል።

“ከቤት ጀምሮ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ መሆን አለበት” ነው ያሉት ሚኒስትሯ፡፡

ቆሻሻ ሲወገድ ሊበሰብሱ የሚችሉና የማይችሉ ተለይተው ለተለያየ ጠቀሜታ ማዋል እንደሚገባም ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ በሀገሪቱ የሚገኙ ከተሞች ልምድ የሚወስዱበትና የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።

ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀክቱ የባሕር ዳር ከተማን የቆሻሻ አያያዝ ያዘምናል ያሉት ደግሞ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳኅሉ (ዶክተር) ናቸው።

ከተማ አስተዳደሩ ለፈሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃም ፕሮጀክቶችን እያፈላለገ መሆኑን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ፕሮጀክቱ ውጤታማና ለአካባቢ ደኅንነት አዋጭ መሆኑን ተናግረዋል። ይህ አይነት ፕሮጀክት በዓለም ላይ ትላልቅ ከተሞችን ደረቅ ቆሻሻ ለመቆጣጠር ያስቻላቸው መሆኑንም ጠቁመዋል። እንደዚህ አይነት ፕሮጀክቶች መኖራቸው የኢትዮጵያና የጃፓንን ግንኙነት ይበልጥ ያጠናክረዋል ብለዋል።

ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here