በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ሕግን የማስከበሩ ዘመቻ ውጤታማ ለውጦች ማምጣቱን የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡

124

ባሕር ዳር: ሰኔ 16/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ላለፉት ጊዜያት ሕገ ወጥ ተግባራት የባሕር ዳር ከተማን ሲፈትኗት እና ነዋሪዎቿን ሲያማርር ቆይቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የከተማዋ ነዋሪዎች ሕግ እንዲከበር ደጋግመው መጠየቃቸውን ተከትሎ ወደ እርምጃ በመገባቱ አበረታች ለውጦች ተገኝተዋል ነው የተባለው፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኅላፊ ኮማንደር አትንኩት አያሌው ለአሚኮ በሰጡት መግለጫ ፖሊስ ሕግ ማስከበር ከመጀመሩ በፊት ራሱን በደንብ አይቷል ብለዋል፡፡ ከሕዝቡ የሚነሱ አስተያየቶችን እና የቀረቡ የግምገማ ውጤቶችን መሰረት አድርጎ የአሠራር ማሻሻያዎች ተደርገው ነበር ያሉት ኮማንደር አትንኩት ከማሻሻያዎቹ በኋላ ወደ ሥራ በመግባት መሰረታዊ ለውጦች መጥተዋል ብለዋል፡፡
ከግንቦት 1/2014 ዓ.ም ጀምሮ በከተማዋ የተጀመረው ሕግ የማስከበር እርምጃ ባሕል እስኪመስል ድረስ ተዘውትሮ የነበረውን የጥይት ተኩስ በማክሰም መሰረታዊ ለውጦችን አሳይቷል ብለዋል፡፡ በስርቆት ተሰማርተዋል የሚል መረጃ የቀረበባቸውን 32 ተጠርጣሪ ባጃጆችን በመያዝ የመረጃ ማጣራት ሥራዎች በመጀመራቸውም በርካታ በስርቆት እና በዘረፋ ተግባራት ተሰማርተው የነበሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ ተጀምሯል ብለዋል፡፡
ሕገ ወጥ ግንባታዎችን እና ኮንቴነሮችን በማፍረስ ሕግ ማስከበር እና የከተማዋን ገጽታ የመመለስ ሥራ መሠራቱን ያወሱት ኮማንደር አትንኩት ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በስርቆት፣ በዝርፊያ እና በግድያ ወንጀሎች ተፈርዶባቸው ነገር ግን በሕግ ቁጥጥር ስር ያልዋሉና በተጨማሪ ወንጀሎች ተሳታፊ የነበሩ ሕገ-ወጦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከማንደሩ ገልጸዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የሕግ ማስከበር ተግባር ልዩ የሚያደርገው አይነኬ እና በልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ራሳቸውን ደብቀው ሕዝብ ሲረብሹ የነበሩ ሕግ ወጦችን መያዝ በመጀመሩ ነው ያሉት ኮማንደሩ ለበርካታ ጊዜ መዝገባቸው ተዘግቶ እና ተድበስብሶ የቆዩ የወንጀል ፋይሎች እንደገና ማየት መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡ ኮማንደር አትንኩት በከተማ አስተዳሩ ውስጥ ባለቤቶችን በማገት ከተሰረቁ ስምንት ተሽከርካሪዎች ውስጥ ሰባቱ መያዛቸውን እና መመለሳቸውንም ገልጸዋል፡፡
ፖሊስ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሕግ ለማስከበር እና የከተማዋን ነዋሪዎች ሰላም ለመመለስ ቁርጠኛ አቋም ወስዷል ተብሏል፡፡ ሕግ የማስከበር እርምጃው በአጠቃላይ ሲታይ ስኬታማ መኾኑንም መምሪያ ኅላፊው ገልጸዋል፡፡
የፖሊስ ሥራ ከሕዝብ ድጋፍ ውጭ ውጤታማ አይኾንም ያሉት ኮማንደሩ ጥቆማ በማድረስ፣ ከጸጥታ ኅይሉ ጋር በትብብር በመሥራት፣ ምስክር በመኾን እና አካባቢን ነቅቶ በመጠበቅ ተባባሪ መኾን አለበት ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/