ባሕር ዳር:መጋቢት 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በድርቅ ተጽዕኖ ስር በሚገኙት የሀገሪቱ አካባቢዎች ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች እየተስፋፉና እየተጠናከሩ እንደሚሄዱ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ኢንስቲስዩቱ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በላከው መግለጫ እንዳሳወቀው፤ በአሁኑ ወቅት በድርቅ ተጽዕኖ ስር በሚገኙት በደቡብ እና በደቡብ ምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች እየተስፋፉ መሆናቸውን የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተለይም በልግ አብቃይ በሆኑ ሥፍራዎች የበልግ ወቅት ዝናብ ያገኛሉ፡፡
በምስራቅ አማራ፣ በሰሜንና ደቡብ አፋር፣ በነገሌ ቦረና፣ በዶሎመና፣ በሜጋ፣ በያቤሎ፣ በሞያሌ እንዲሁም ጥቂት የሶማሌ ክልል ዞኖች ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ፡፡ የተቀሩት የሀገሪቱ አካባቢዎች በአመዛኙ ደረቅ ሆነው ይሰነብታሉ ተብሏል።
በአጠቃላይ ከኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢሉአባቦራ፣አርሲና ባሌ፣ ቦረናና ጉጂ፤ምዕራብና ሰሜን ሸዋ፤ ምስራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ፤ ሐረሪ ክልል፤ ድሬዳዋ፤ አዲስ አበባ፤ ከጋምቤላ የማጃንግ ዞን፤ ከአማራ ክልል ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ፤ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራቸዋል፡፡
ከትግራይ ክልል የደቡብና የምሥራቅ ትግራይ ዞኖች፤ ከአፋር ክልል ዞን 3፣ 4 እና 5፤ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ዞኖች፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፤ የሲዳማ ክልል ዞኖች እንዲሁም ከሶማሌ ክልል አብዛኛው ዞኖች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡
በሌላ በኩል የሀገሪቱ ቆላማ ሥፍራዎች ላይ የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት ከ35 ድግሪ ሴልሽየስ በላይ የሙቀት መጠን እንደሚኖራቸው የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!