በሰሜን ጎንደር ደጋማ ወረዳዎች የበረሃ አንበጣ ተከሰተ፡፡

0
145

በሰሜን ጎንደር ዞን ደጋማ ወረዳዎች ማለትም በየዳ፣ ጠለምትና ጃናሞራ ወረዳዎች የበረሃ አንበጣ መንጋ መከሰቱ ተገለጸ።

የአንበጣ መንጋው በዞኑ ሦስቱም ወረዳዎች የካቲት 28 ቀን ጀምሮ መታዬቱን የሰሜን ጎንደር ዞነ ግብርና መምሪያ የኤክስቴንሽን ቡድን መሪ አቶ ዋለ መርሻ  ተናግረዋል፡፡ ባለሙያው እንዳሉት የበረሃ አንበጣ መንጋው በሦስቱ ወረዳዎች በሚገኙ ስምንት ቀበሌዎች ነበር የተከሰተው፤ በሂደት ግን አድማሱን በማስፋት በሦስቱም ወረዳዎች በ32 ቀበሌዎች ላይ ተስፋፍቷል።

የበረሃ አንበጣ መንጋው አሁን ላይ የሰብል ወቅት ባለመሆኑ ጉዳት አለማድረሱን የገለጹት አቶ ዋለ የመስኖ ሰብሎች ለይ ጥፋት እንዳያደርስ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ኅብረተሰቡ የሰብል ወቅት አለመሆኑን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ቸልተኝነት ማሳዬቱን ያመለከቱት ባለሙያው የበረሃ አንበጣ መንጋው ተመቻችቶ ከተቀመጠ እንቁላል ሊጥል ስሚችል ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በባህላዊ ዘዴ ቆርቆሮ እና ጅራፍ በማጮህ ለማባረር ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝና በመሬት ላይ እንዳያርፍ የመከላከል ሥራ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት አቶ ዋለ ወደ ተራራማው አካባቢ ሲንቀሳቀስ በባህላዊ ዘዴ መከላከሉን አስቸጋሪ ማድረጉን አመልክተዋል።

የበረሃ አንበጣ መንጋው ባልተከሰተባቸው አካባቢዎች ባሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ንቅናቄ በመፍጠር አስቀድሞ ለመከላከል እየተሠራ እንደሆነም ገልጸዋል።

የበረሃ አንበጣ በቆላማ አካባቢዎች እንደሚከሰት ቢታወቅም በሰሜን ጎንደር የተከሰተባቸው ሦስቱ ወረዳዎች በአብዛኛው ደጋማ ናቸው፡፡ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የበረሃ አንበጣ መንጋ መኖሩን አብመድ መረጃዎች እየደረሱት ነው፤ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የተለያዩ ወረዳዎችም መከሰቱ ተሰምቷል፡፡ ከዚህ ቀደም በደቡብና ሰሜን ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ምዕራብና ምሥራቅ ጎጃም ዞኖችና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር መከሰቱ ይታወሳል፡፡

ዘጋቢ፡- ደስታ ካሳ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here