ደብረ ብርሃን:መጋቢት 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ በሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማ በር ወረዳ ግዙፍ የመስኖ ፕሮጀክት ሊያስገነባ ነው።
ፕሮጀክቱ 273 ሚሊዮን 576 ሺህ 474 ብር ወጪ ይደረግበታል። ከ 450 ሄክታር በላይ መሬት ማልማት የሚችል ሲሆን 350 አባውራዎችን ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተገልጿል።
የመስኖ ፕሮጀክቱን ዓባይ የግንባታ ተቋራጭ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሚያከናውነው ይሆናል። በ25 ወራት ውስጥ ግንባታው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ እንዲሆንም ቀጠሮ ተይዞለታል። የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር የግንባታውን የስምምነት ሰነድ ርክክብ ፈጽሟል።
የጣርማበር ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ሳሙኤል መርሻ ፕሮጀክቱ የሕዝቡን የዘመናት የመልማት ጥያቄ የመለሰ ነው ብለዋል። የግብርና ምርትን በማሳደግ ምጣኔ ሀብታዊ መነቃቃት ይፈጥራልም ተብሏል። ዋና አሥተዳዳሪው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የወረዳው አሥተዳደርና ሕዝብ አቅሙ የቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን 70 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ የመልማት አቅም እንዳለው በጥናት ተረጋግጧል። በተጨባጭ እየለማ ያለው ግን 29 ሺህ ሄክታር ብቻ ነው። ከዞኑ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት መመሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በዞኑ ያለውን በመስኖ የመልማት አቅም አሟጥጦ ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው።

በተያዘው ዓመት ብቻ በግንባታ ሂደት ላይ ያሉና በአዲስ የሚሰሩ 27 የመስኖ ፕሮጀክቶች ስለመኖራቸውም የመምሪያው ኀላፊ ችሮታው አስፋው ተናግረዋል። ከእነዚህ መካከል ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥረው የአዋዲ መስኖ ፕሮጀክት አንዱ ሲሆን በተያዘለት የጊዜ ቀጠሮ በጥራት እንዲጠናቀቅም ጥብቅ ክትትል ይደረጋል ብለዋል።
በዓባይ የግንባታ ተቋራጭ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የግንባታ ክትትል የሥራ ሂደት መሪው መላክ አለለኝ የመንገድ መሠረተ ልማት እና የግንባታ ግብዓት አቅርቦት ችግሮች ፈተና ሊሆኑ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። ሆኖም ችግሮችን በመፍታት ፕሮጀክቱ በጥራትና በጊዜው እንዲጠናቀቅ ይደረጋል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ደጀኔ በቀለ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!