በሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የተከሰተው የጸጥታ ችግር አንጻራዊ ሰላም እያሳየ መሆኑን አስተዳደሮቹ ገለጹ፡፡

477

በሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የተከሰተው የጸጥታ ችግር አንጻራዊ ሰላም እያሳየ መሆኑን አስተዳደሮቹ
ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 14/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር በተፈጠረ
የጸጥታ ችግር የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ አካል ጎድሏል፣ ንብረት ወድሟል፣ ነዋሪዎችም በስጋት ውስጥ እንዲቀመጡና ከቀያቸው
እንዲለቁ ሆነዋል፡፡ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የጸጥታ አካል ወደ አካባቢው በመግባት የማረጋጋት ሥራ እየሠራ መሆኑን
መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የአካባቢውን ውሎ በተመለከተ የሁለቱ አስተዳድሮች አስተዳዳሪዎች ለአብመድ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ታደሰ ገብረጻዲቅ የዛሬው ውሎ ትናንት ከነበረው የተሻለ፣ ችግሩን የመቆጣጠርና የመቋቋም
ሁኔታ አለ ብለዋል፡፡ ችግሩን ለመቆጣጠር ሰፋፊ ሥራዎች መሰራታቸውንም ተናግረዋል፡፡ የአካባቢው፣ የክልሉና የፌደራል የጸጥታ
መዋቅር በጋራ በመሆን ችግሮችን ለመቆጣጠር በተሰራው ሥራ አንጻራዊ ሳለም አለ፤ ነገር ግን አሁንም ስጋቱ አለ ነው ያሉት፡፡
በተጀመረው አግባብ መሥራት ከተቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁኔታውን መቆጣጠር እንደሚቻልም አስታውቀዋል፡፡
ከተፈጠረው ችግር አንጻር በማኅበረሰቡ ዘንድ አለመረጋጋት እንዳለ ያስታወቁት ዋና አስተዳዳሪው በተለይም ሸዋ ሮቢት አካባቢ
አለመረጋት መኖሩንም ተናግረዋል፡፡ ማኅበረሰቡን ለማረጋጋት እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም ሥራዎች እየተሰሩ
ናቸውም ብለዋል፡፡
ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የተኩስ ልውውጥ አለመኖሩንም አስታውቀዋል፡፡ የተኩስ ልውውጥ የለም ማለት ችግሩ
ቆሟል ማለት አይደለም ያሉት ዋና አስተዳደሪው ማኀበረሰቡን ለማረጋጋት የጸጥታ መዋቅሩ በጋራ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
ሕዝብ የችግሩ መነሻም መዳረሻም አይደለም፣ በሥራ ላይ እያለ ነው ችግሩ የተከሰተበት፣ ይህን የፈጸሙት ደግሞ በሕዝብ
ውስጥ ገብተው የራሳቸውን ጥቅም ለማሳካት የሚፈልጉ ኀይሎች ናቸው፣ የተሸረበውን ሴራ በማጋለጥ በጋራ በመሆን አጥፊውን
ኃይል ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ መስራት ይገባናልም ብለዋል፡፡ ችግሩ ተመልሶ እንዳይመጣ አካባቢውን የማፅዳት፣ በእኩይ
ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ አካላትን ተጠያቂ የማድረግና ሕዝቡ ተናቦ እንዲሰራ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ የየአካባቢው
ማኅበረሰብም የተለየ ነገር ሲያይ ጥቆማ በመስጠትና ራሱን በማረጋጋት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡
የተጀመረውን ሁኔታ በአጭር ጊዜ የበለጠ ወደ ጥሩ ሁኔታ እናመጠዋለን፤ ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ጋርም በጋራ እየሰራን
ነው ብለዋል፡፡
የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳደሪ አህመድ ሀሰን በአካባቢው ካለፉት ቀናት ዛሬ አንጻራዊ ሰላም ታይቷል ብለዋል፡፡
በተለይም ከሚሴ አካባቢ ትናንት እና ከዚያ በፊት ከነበረው አንጻር ሰላማዊ ሁኔታ ነው ያለው ብለዋል፡፡ አርጡማ ፉርሲ አካባቢ
የነበረው የፀጥታ ችግር ዛሬ ወደሰላማዊ ሁኔታ ተመልሷል ብለዋል፡፡ ጅሌ ጥሙጋም አንጻራዊ ሰላም አለ ነው ያሉት፡፡ አካባቢውን
ለማረጋጋት የጸጥታ ኃይል መግባቱንም ተናግረዋል፡፡ የገባው ኃይል በጥምረት እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ የሚነዙ
አሉባልታዎች ማኅበረሰቡ እንዳይረጋጋ እያደረጉት መሆናቸውንም ነው አቶ አሕመድ የተናገሩት፡፡
ሕዝቡ እንዲረጋጋ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፤ የጸጥታ ኃይሉ በመቆጣጠር፣ በመከታተልና
እርምጃ በመውሰድ መልካም የሚባል ሥራ እያከናወነ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችንና
ተሰሚነት ያላቸውን ሰዎች ለማነጋገር ጥረት እየተደረገ ነውም ብለዋል፡፡
በብሔረሰብ አስተዳደሩ አልፎ አልፎ ተኩስ ያለባቸውን አካባቢዎች ለማስቆም የጸጥታ ኃይሉ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡ ሕዝቡ
እንዲረጋጋ የጸጥታ አካሉ የተቀናጀ ሥራ መስራት እንደሚገባው፣ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እውነትን ማዕከል ያደረገ፣ ለሕዝብ
ተስፋ የሚሰጥና የሚያረጋጋ መግለጫ በመስጠት፣ የታችኛው የሥራ ኃላፊም የሚያስተዳድረውን ሕዝብ በአግባቡ ማገልገል
አለበት ነው ያሉት፡፡ ሰው እንዳይሞት ጠንካራ ሥራ መሠራት አለበትም ብለዋል፡፡ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች
እያደረጉት ያለውን መልካም ሥራ ከቀጠሉበት አካባቢው ከስጋትና ከጥርጣሬ ወጥቶ የተሻለ ሰላም ይሆናል ብለዋል፡፡
አቶ አሕመድ ከሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ጋር ከችግሩ መፈጠር አስቀድሞ በጋራ ሲሰሩ እንደነበርና አሁንም በጋራ እየሰሩ
መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ ለመገናኘት አስቸጋሪ ቢሆንም ሁኔታውን ለማስቆም ስራዎች እንደተሰሩም
ተናግረዋል፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው ወሬ መቆም ይገበዋልም ነው ያሉት፡፡ ሁሉም ራሱን ለሰላምና ለአንድነት ማዘጋጀት አለበት
ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m