“በሦስተኛ ወገን የሚጓተት የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት እንዳይኖር ችግሮችን ፈትተናል” የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር

57
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ

ባሕርዳር: ጥር 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር እና ዙሪያው የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅ የመልካም አስተዳደር ችግር ኾኖ ቆይቷል፡፡ በተጨማሪ በመንግሥት በጀት ላይም ያሳረፈው ጫና ቀላል እንዳልኾነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ከሚገነቡ የፌደራል መንግሥት የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል ከሰባታሚት ጭስ ዓባይ ያለው የ21 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር አስፓልት መንገድ ግንባታ አንዱ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ 2010 ዓ.ም ላይ የመሰረት ድንጋዩ ሲቀመጥ በሦስት ዓመታት ለማጠናቀቅ ነው። 2012 ዓ.ም የተጀመረው ግንባታዉ እስካሁን ድረስ ከ30 በመቶ በላይ መሄድ አልቻለም ተብሏል፡፡

የባሕር ዳር ጢስ እሳት መንገድ ሥራ ፕሮጀክት ሥራ አሥኪያጅ ኢንጅነር ሰለሞን ወልደ ገብርኤል ለፕሮጀክቱ መጓተት መሰረታዊ ችግር ከሦስተኛ ወገን ነጻ አለማድረግ ነበር ብለዋል፡፡ የፕሮጀክት ጊዜው በመጠናቀቁ ተጨማሪ ጊዜ ይሰጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፡፡

ኢንጅነር ሰለሞን 21 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን ፕሮጀክት ለመገንባት ውል የተያዘው በ957 ሚሊየን ብር ነበር ብለዋል፡፡ ውል በወሰድንበት ጊዜ የነዳጅ ዋጋን እንደምሳሌ ብናይ የአንድ ሊትር ነዳጅ ዋጋ 18 ብር ነበር የሚሉት ሥራ አስኪያጁ አሁን የአንድ ሊትር የነዳጅ ዋጋ 68 ብር ደርሷል ነው ያሉት፡፡

እንደ ሥራ አስኪጁ ገለጻ በአሁኑ ወቅት ለግንባታ የሚያስፈልገው ጠቅላላ ወጪ 130 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ ከ21 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ውስጥ ወደ 15 ኪሎ ሜትር የሚደርሰው ከሦስተኛ ወገን ነጻ ሆኗል ተብሏል፡፡ ቀሪውን ስድስት ኪሎ ሜትሮች ደግሞ የምዕራብ ጎጃም አሥተዳደር በቀጣይ ጊዜያት ነጻ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት ኢንጅነር ሰለሞን፡፡

እስከ መጪው ሰኔ ወር ፕሮጀክቱ እስከ 70 በመቶ ሠርቶ ለማጠናቀቅ እየተንቀሳቀሱ መኾኑን ያነሱት የፕሮጀክቱ ሥራ አሥኪያጁ ከሦስተኛ ወገን ነጻ ማድረግ በተጨማሪ በሀገር ደረጃ የሚስተዋለው የሲሚንቶ አቅርቦት እጥረት እንዲፈታ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡

ከሰባታሚት ጭስ ዓባይ እና ከባሕር ዳር ዘጌ የሚሠሩት የፌደራል መንግሥት የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶች ከተቀመጠላቸው ጊዜ አንጻር ሲታይ የዘገየ አፈጻጸም የታየባቸው ነበሩ ያሉን የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶ•ር) ናቸው፡፡ ለፕሮጀክቶቹ መዘግየት ዋና ምክንያት ከሦስተኛ ወገን ነጻ አለማድረግ እንደኾነም አንስተዋል፡፡

ከተማ አሥተዳደሩ ከሦስተኛ ወገን ነጻ አለማድረጉ መሰረታዊ ችግር እንደነበር ገምግሟል ያሉት ዶክተር ድረስ “በሦስተኛ ወገን የሚጓተት የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት እንዳይኖር አድርገን ችግሮችን ፈተናል” ብለዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በከተማ አሥተዳደሩ ውስጥ የሚፈጠር የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት መጓተት ቢኖር የተቋራጮች እንጂ የከተማ አሥተዳደሩ አይኾንም ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!