ባሕር ዳር: ግንቦት 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሞሮኮ ማራካሽ ከግንቦት 23 እስከ 25 /2015 በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ ስምንት ጀማሪ የሥራ ፈጣሪዎች (ስታርርትአፖች) እንደሚሳተፉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ኢትዮጵያ በአውደ ርዕዩ ላይ ስትሳተፍ የዘንድሮው ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
በአውደ ርዕዩ የሚሳተፉት የስራ ፈጣሪ ድርጅቶች ዛሬ ሽኝት ተደርጎላቸዋል።
በሽኝቱ ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ፒ ኤች ዲ) የተገኙ ሲሆን ስራ ፈጣሪዎቹ ከሚኒስትሩ ጋር ተወያይተዋል።
አውደ-ርዕዩ የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪዎች እና በዲጂታል ንግድ ስራዎች የሚሠሩ ተቋማት እንደሚሳተፉበት ገልጿል።
ስምንት ጀማሪ የስራ ፈጣሪ ድርጅቶች(ስታርርትአፖች) የተለዩት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባወጣው ማስታወቂያ ተወዳድረው መሆኑም ተመላክቷል።
የጃፓን ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ(ጃይካ) ለተሳታፊዎቹ ድጋፍ እንደሚያደርግ ሚኒስቴሩ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መረጃ ገልጿል።
ሥራ ፈጣሪዎቹ ኢትዮጵያን ወክለው ያሏቸውን ስራዎች ለኢንቨስተሮችና ሌሎች ታዳሚዎች እንደሚያቀርቡና በተለያዩ የውይይትና ምክክር መድረኮች ላይ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ አመልክቷል።
የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ከሌሎች አገራት ከመጡ የመንግስት ተወካዮች፣ ሌሎች ኢትዮጵያን ወክለው የሚገኙ ተሳታፊዎችና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር የተለያዩ ውይይቶች እንዲሁም የቴክኖሎጂ ጉብኝቶች እንደሚደረግም ተጠቁሟል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ሁሉም ተሳታፊዎች ኢትዮጵያን በሚገባት ደረጃ መወከሏን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎችን ማቅረብ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
በአውደ ርዕዩ የተፈጠረውን እድል በአግባባቡ መጠቀምና በቀጣይም መሰል ተሳትፎዎችን በይበልጥ በማጠናከር ማስፋት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
በአውደ ርዕዩ ላይ ሥራ ፈጣሪዎቹ እንዲሳተፉ ላዳረጉ አካላት፣የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የምርምር ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ.ር) የተመረጡት ሥራ ፈጣሪዎች በውጤታማ ሥራቸው የሚታወቁ ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችና ኩባንያዎች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!