በማይካድራ በአሸባሪው ትህነግ ሰርጎ ገቦች ላይ የማያዳግም እርምጃ መወሰዱን የወረዳ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡

0
234

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 14/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ማይካድራ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች እድል ቢያገኙ በአማራ ሕዝብ ላይ ምን ማድረግ እንደሚፈልጉ ያሳየ አሳዛኝ ጭፍጨፋ የተካሄደባት ከተማ ናት፡፡ አካባቢው ለሱዳን ድንበር ቅርብ ከመሆኑም በላይ የኢትዮጵያን በጎ የማይመኙ የውጭ ኀይሎች እና የውስጥ ጉዳይ አስፈፃሚዎቻቸውን ትኩረት ይስባል፡፡ አሸባሪው የትህነግ ቡድን ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም በአንድ ሌሊት ብቻ በሺህ የሚቆጠሩ ንጹሐንን በአሰቃቂ ሁኔታ ጨፍጭፎ የወጣው በዚሁ አካባቢ ነበር፡፡

ከሁመራ ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ማይካድራ የከተማዋን እና የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የጸጥታ ኀይሎች ቅንጅት በአስተማማኝ ቁመና ላይ መሆኑን አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

ወጣት አበበ ገላነህ የማይካድራ ከተማ ነዋሪ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ በተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ ገብቶ አካባቢውን በንቃት እየጠበቀ መሆኑን ነግሮናል፡፡

ማይካድራ ከመላ ሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ዜጎች ለሥራ የሚገቡባት ከተማ ናት ያለን ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት አበበ አለባቸው ነው፡፡ በኬላ ፍተሻ፣ በሥራ አካባቢዎች ቅኝት፣ በከተማ አካባቢዎች ልዩ እንቅስቃሴ እና በበርሃ አካባቢ ባሉ የሥራ ቦታዎች ሳይቀር በቂ ክትትል እየተደገረ መሆኑን ገልጿል፡፡

የማይካድራ ወረዳ ሰላም እና ሕዝብ ደኅንነት ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኅላፊ ሻምበል ደምለው ፈንታው የአካባቢውን ጸጥታ አስተማማኝ ለማድረግ በቂ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡

መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ ሰላም አስከባሪ ሕዝባዊ ሠራዊት፣ ፋኖ እና ወጣቶች በተደራጀ መልኩ አካባቢውን በንቃት እየጠበቁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ሽብርተኛው ትህነግ የውጭ ኀይሎች በሚሰጡት ስምሪት በአካባበቢው በተደጋጋሚ ሰርጎ ለመግባት ሙከራ እንዳደረገ ሻምበል ደምለው አንስተዋል፡፡ በተደራጀ መንገድ በመጡ ሰርጎ ገቦች ላይ በተቀናጀ ኦፕሬሽን የማያዳግም እርምጃ ተወስዷል ብለዋል፡፡

የሽብርተኛው ትህነግ ቡድን በተለያየ ጊዜ እየተቆራረጠ ለመግባት ቢሞክርም የጥፋት ዓላማውን ማሳካት እንዳልቻለ እና ወደፊትም ማሳካት እንደማይችል ነው ሻምበል ደምለው የገለጹት፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከማይካድራ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here